
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በልማት የሚነሱ 138 ግለሰቦችን በመለየት ሕጋዊ የፕላን ቤት የሚገነቡበትን ቦታ ለማስረከብ የእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ሥራ አሥኪያጅ ተሻገር አዳሙ ባሕር ዳር ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ፤ ለጎብኝዎች ሳቢ እንድትኾን በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናዎኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ከተማዋ ጣና ሐይቅን እና የዓባይን ወንዝ ይዛ ማኅበረሰቡ ግን በአግባቡ የሚዝናናባቸው ቦታዎች በሚፈለገው ሁኔታ አለመልማታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም በኮሪደር ልማቱ ጣና ሐይቅን አብዝቶ የመግለጥ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በዋና ዋና የከተማዋ ግራ እና ቀኝ የአስፋልት መንገዶች ዳርቻ የሚገኙ ሕንጻዎችን በቀለም የማስዋብ እና በመብራት የማስጌጥ ሥራ እየተከናዎነ መኾኑን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ ሲሠራ እና የጣና ሐይቅ ሲገለጥ ከ10 ሄክታር በላይ ክፍት ቦታዎች ተገኝተዋል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ በድብ አንባሳ እና ሰመር ላንድ ሆቴሎች መካከል እስከ ዋተርፍሮንት ሆቴል ድረስ ስፋቱ 40 ሜትር እና ርዝመቱ 780 ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል፡፡
መንገዱ በሚያልፍበት ቦታ ላይም በቀበሌ የኪራይ ቤት የሚኖሩ ግን ሕጋዊ ቦታ በስማቸው የሌላቸው 138 ግለሰቦች ተለይተው ለእያንዳንዳቸው 100 ካሬ ሜትር ሕጋዊ የፕላን ቤት መሥሪያ ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል ነው ያሉት። ቦታዎችንም ለልማት ተነሽዎች በዕጣ የማስተላለፍ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተካሄዷል፡፡
በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ወንዳለ ጋሻው መንገዱን ለመገንባት ከታቀደ ብዙ ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል። የልማት ተነሽዎች ከታኅሳስ ወር ጀምሮ እንደሚነሱ ተነግሯቸው መቆየቱን አንስተል። ከልማት ተነሺዎች ጋር ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል።
ከተነሽዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ የሚረከቡትን ቦታ እንዲያዩት በማድረግ ይሁንታቸውን ገልጸዋል ያሉት ምክትል ሥራ አሥኪያጁ የውኃ፣ መብራት፣ መንገድ እና ሌሎችም መሠረተ ልማታዊ ጉዳዮች ይሟላላቸዋል ነው ያሉት።
መንገዱ የኮሪደር ልማቱ አንዱ አካል በመኾኑ ሥራው በፍጥነት መከናወን አለበት ነው ያሉት፡፡ ተነሽዎች ሥራው ቶሎ እንዲጀመር ያለተጨማሪ ጊዜ ቦታውን ለልማቱ በመልቀቅ ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ሕጋዊ የመኖሪያ የፕላን ቤት መሥሪያ ቦታ በዕጣ ያገኙት አባት አርበኛ ተክሉ በርሄ በማምሻ እድሜየ የት እወድቃለሁ እያልሁ ስጨነቅ መንግሥት ቦታ ስለሰጠኝ ደስ ብሎኛል ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ ተጠቃሚ ወይዘሮ የሽዋ አስፋው ከቀበሌ ቤት ወጥቼ የራሴ ቤት እንዲኖረኝ በመደረጉ እና በከተማዋ የልማት ሥራው ደስተኛ ነኝ ነው ያሉት፡፡ ለመነሳት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ወይዘሮ አድና በላይ እኛ ለልማት አካባቢውን ስንለቅ መንግሥት ደግሞ በሚሰጠን ቦታ ላይ በልዩ ሁኔታ መሠረተ ልማቱን ሊያሟላልን ይገባል ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!