አዲስ አበባ አፍሪካ መለወጥ እንደምትችል እያሳየች ያለች ከተማ መኾኗን የውጭ ዜጎች ተናገሩ።

25

አዲስ አበባ፡ መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎አዲስ አበባ በአፍሪካ ቀዳሚ የኮንፈረንስ መዳረሻ እየኾነች መጥታለች። የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ የኾነችው አዲስ አበባ በርካታ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።

መንግሥት በሀገሪቱ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት ባሻገር በሀገሪቱ የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ቅርሶችን በማደስም የሀገሪቱን ገጽታ እየለወጠ ነው። ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የእንግሊዝኛ ዝግጂት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የኤፍ ኤች ኢትዮጵያ ተወካይ ሞሰስ ዶምቦ (ዶ.ር) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ የከተማዋን ገጽታ እያጎላው መኾኑን ይናገራሉ።

ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት በ1986 እንደኾነ የሚናገሩት ዶክተር ሞሰስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ገባ ወጣ እያሉ እየጎበኙ መቆየታቸውን እና አሁን አዲስ አበባ እየኖሩ እና ሥራ እየሠሩ እንደኾነም ተናግረዋል። በእርግጠኝነት የአዲስ አበባ ከተማ ለውጥ እዚህ ለሚመጡት ሁሉ ግልጽ ነው ሲሉ የከተማዋን ለውጥ መስክረዋል። በኮሪደር ልማቱ የተነሳ መንገዶቹም ስለመስፋታቸው ነው የተናገሩት። በከተማው ውስጥ በምሽት መኪና ሲነዱ የተለዬ ድባብ ያለው እና አስደናቂ ስለመኾኑም አብራርተዋል።

ዶክተር ሞሰስ መንግሥት ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ከመፍጠር ባሻገር ለጎብኝዎች ተስማሚ እና አስደናቂ ፓርኮችን ገንብቷልም ብለዋል። በመንግሥት የተገነቡ ድንቅ ፓርኮችን መጎብኘት እንደሚወዱም አብራርተዋል። እንደ እንጦጦ፣ የወዳጅነት መናፈሻ እና ጉለሌ ፓርኮችን እንደጎበኙም ጠቁመዋል።
እነዚህን ፓርኮች ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች በመኾናቸው ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

መንግሥት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመገንባት በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ብሎም የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት እንደሚያስችለውም ዶክተር ሞሰስ ገልጸዋል። የቱሪስት መዳረሻዎቹ ኢንቨስተሮች እና ባለሃብቶች በሀገሪቱ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ እንደኾኑም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የጀመረቻቸው ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በአፍሪካ ቀንድ ተጨባጭ ሁለንተናዊ ለውጦችን ማምጣት እንደምትችል ማሳያ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት። አፍሪካዊ ነኝ፤ የተለወጠች አፍሪካን ማየት እመኛለው፤ በእርግጠኝነት አፍሪካ ማድረግ የሚያስችል አቅም አላት፤ ለዚህም አዲስ አበባ ማሳያ ናት ነው ያሉት ።

ዘጋቢ: ብርሃኑ ወርቅነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ያገኘው ነጻነት የሀገራዊ ለውጡ ታላቅ ትሩፋት ነው።
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ለልማት ተነሽዎች የቤት መሥሪያ ቦታ ለማስተላለፍ የእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት አካሄደ።