
ሁመራ: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ትናንትን፣ ነገን እና ዛሬን በማስተሳሰር የሀገራችንን ልዕልና እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሕብረት አባላት ውይይት አድርገዋል።
ሕብረቱ የሀገራዊ ለውጡን ሰባተኛ ዓመት እና የዞኑን የነጻነት ጉዞ አራተኛ ዓመት ትሩፋቶችን ለመዘከር በማሰብ ነው በሁመራ ከተማ ውይይት ያካሄደው። እንደ ሀገር ፓርቲው አካታች የፖለቲካ ምኅዳር በመፈጠር አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያና የብልጽግና ሕብረት የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ ፍስሃ ሃጎስ ተናግረዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ነጻነት የሀገራዊ ለውጡ ታላቅ ትሩፋት መኾኑን ያነሱት አቶ ፍስሃ ከ2010 ዓ.ም በፊት “አማራ ነኝ” የሚል አቋም የያዙ ወገኖች ብዙ ግፍ ይደርስባቸው ነበር ብለዋል። ብዙዎች ተገድለዋል፤ ብዙዎች ተሰውረዋል፤ ብዙዎችም ታሥረው ነበር፤ ለውጡን ተከትሎ ግን የታሠሩት መፈታት እና የዞኑ ነጻነትም የተረጋገጠበት ታላቅ አጋጣሚ መኾኑን አስረድተዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት የዘመናት የነጻነት ጥያቄው የተመለሰው የዞኑ ሕዝብ የለውጡ መንግሥት ደጋፊ እና የብልጽግና ፓርቲ መሥራች በመኾን ሀገር የምትጠብቅበትን ኀላፊነት በመወጣት የሀገርን ልዕልና ለማረጋገጥ የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል። ባለፉት አራት የዞኑ የለውጥ ዓመታት ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ ከሕዝብና ከውስጥ ገቢ በመሰብሰብ የመሠረተ ልማት ሥራ መከናወን መቻሉን አንስተዋል።
ሕብረቱ ባስቀመጠው አንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀከት የልማት አቅጣጫ መሠረት በተያዘው በጀት ዓመትም ከ250 ሚሊዮን በላይ በኾነ በጀት እየተሠራ ነው ብለዋል። ለአሠራር፣ ለአገልግሎት አሰጣጥ እና እንደ ዜጋ ተጠቃሚ ለመኾን የዲጂታል መታወቂያ ለዞኑ ማኅበረሰብ የሚሰጥበት ሥርዓት አለመፈጠሩ ትልቅ ችግር ኾኗል ነው ያሉት።
የፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት ለማግኘት እንደ ሀገር አስገዳጅ እየኾነ በመጣበት ኹኔታ የዞኑ ሕዝብ መታወቂያውን ማግኘት የሚችልበት አማራጭ አለመኖሩ ሕዝቡ ጥያቄ እንዲያነሳ ማድረጉን ጠቁመዋል።
መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ለመዘከር እና የለውጡን ትሩፋቶች ለመገምገም ዓላማ ያደረገው የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ሕብረት ውይይት መልካም ተግባሮችን በማስቀጠል እና ተግዳሮቶችን በማረም ማስቀጠል እንደሚገባ ግንዛቤ በመፍጠር ተጠናቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን