
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተመካከሩ ችግሮቻቸውን ፈትተዋል። አለመግባባቶቻቸውን ቀርፈዋል። አንድነታቸውን አጠንክረዋል። የተመካከሩ ተግባብተዋል። ተሳስረዋል። እንደ ዓለት ጠንክረዋል። ለሀገራቸውም የተሻለውን ሃሳብ መርጠዋል። ሀገራቸውን በተሻለው ሃሳብ መርተዋል። አሳድገዋል።
መመካከር ደም መፋሰስን ታስቀራለች። ቂም እና በቀልን ታርቃለች። አለመተማመንን በመተማመን ትተካለች። ፍቅር እና ሰላምን ታመጣለች። ተድላ እና ደስታን ታደረጃለች። ያልተመካከከሩ ለዘመናት ተዋግተዋል። ደም ተፋስሰዋል። አጥንት ተከሳክሰዋል። ያልተመካከሩ ሳይተማመኑ ዘመናትን አልፈዋል። ልጆቻቸውን አጥተዋል። የሀገራቸውን ሃብት እና ንብረት አውድመዋል። በዘመናት ሂደት ውስጥም እልፍ ጉዳይ አጥተዋል።
የተመካከሩ የሀገራቸውን ሰላም አጽንተዋል። ልጆቻቸውን በሰላም አሳድገዋል። ሀገራቸው ያላትን ጸጋ በአንድነት እና በፍቅር ተጠቅመው አድገዋል። ለልጅ ልጅ የተመቸች ሀገር አውርሰዋል። ኢትዮጵያውያንም ችግሮቻቸውን በምክክር ለመፍታት ጉዞ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ገናና እና ኀያል ታሪክ ላላት ኢትዮጵያ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ መፍታት የተገባ ነውና። ዓለምን ያስደነቁ ታሪኮችን የሠሩ ኢትዮጵያውያንም ችግሮቻቸውን በምክክር ፈትተው የጋራ ሃሳብ ለመያዝ አይቸገሩም።
“ምንም ቢፈጠር ምንም ቢመጣ ከሽማግሌ ከዕርቅም አይወጣ” እንዳለ የሀገሬው ሰው ከምክክር፣ ከውይይት እና ከንግግር የሚያልፍ የለም። ምንም ቢፈጠር በንግግር ይፈታል። በምክክር ሰላም እና ፍቅር ይጸናል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በምክክር የተመቻቸ ሀገር ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ እየሠራ ነው። ይሄን የምክክር ሂደት በአግባቡ መጠቀም ደግሞ ስኬታማ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። አለመግባባቶቻችን እና ልዩነቶቻችንን በምክክር ፈትተን እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ መሻገር አለብን ይላሉ። ለዘመናት በኅብረተሰቡ፣ በፖለቲከኞች፣ በመሪዎች እና በሌሎች ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን አቅርቦ መወያየት ይገባል ነው የሚሉት። እንደ ሀገር ታላቅ ዕድል ቀርቧል የሚሉት ቃል አቀባዩ ይሄን መጠቀም ደግሞ መልካም ምርጫ እና ብልህነት ነው ይላሉ።
ግጭቶች በየትኛውም ዓለም አሉ፣ ልዩነቱ ግጭቶቹ ምን ያክል ጥልቅ ናቸው፣ የሚፈቱበትስ መንገድ ምን ዓይነት ነው የሚለው ነው ብለዋል። የሃሳብ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ሁለት አማራጮች አሉ። የመጀመሪያው በግጭት የመፍታት ሂደት ነው። ይህ ግን እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላምን የማያመጣ፣ ሀገርን እና ሕዝብን የሚያከስር ብሎም ማባሪያ የሌለው ነው፤ ኢትዮጵያም ለዘመናት ሞክራው ብዙ ነገር አጥታበታለች ነው የሚሉት።
ሁለተኛው የመፍቻ አማራጭ የሃሳብ ልዩነቶችን ተቀብሎ፣ አጀንዳዎችን ወደ ውይይት እና ምክክር አቅርቦ ቁጭ ብሎ ተመካክሮ መፍታት ነው። እንደ ሀገር ልዩነቶችን በኃይል አማራጭ የመፍታት ሂደት በቂ ተሞክሮ አለን የሚሉት ቃል አቀባዩ ብዙ ተሞክሮ የሌለን ችግሮችን ተመካክሮ የመፍታት ጉዳይ ነው ይላሉ።
እንደ ሀገር እና ሕዝብ የትኛው የመፍቻ መንገድ ነው የሚያዛልቀው፣ የትኛውስ ነው ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣው የሚለውን አመዛዝኖ መረዳት ይገባል ነው የሚሉት። በኀይል አማራጭ የሚደረገው ጥረት ምን አልባትም ለጊዜው አንዱን አሸናፊ ሌላኛውን ተሸናፊ ሊያደርግ ይችላል፣ ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት አይፈታም። ምክንያቱም ዛሬ ተሸናፊ የኾነው ነገ ለማሸነፍ ጥረት ማድረጉ ሰላማይቀር ይላሉ።
ምክክር የሚባለው ጉዳይ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ነው። በአንደኛው ወገን ላይ ድልን፣ በሌላኛው ወገን ደግሞ የመሸነፍ ጠባሳን ጥሎ አያልፍምና። በምክክር ሂደት ውስጥ ማንም ተሸናፊ አይኾንም። ሁሉም አሸናፊ ይኾናል እንጂ። እንደ ሀገር ያሉ ችግሮችን ቁጭ ብሎ በመመካከር መፍታት ይገባል ነው የሚሉት።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት ውስጥ ወሳኙ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ነው። ለብቻቸው የሚወስኑ ፖለቲከኞች እና መሪዎች የሉበትም። ሁሉም በአሳታፊነት እና በአካታችነት የሚሳተፍበት ነው ይላሉ። ሁሉም በሀገሩ እጣ ፋንታ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት የምክክር ሂደት መኾኑንም አንስተዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም የሚያሳትፍ እና የሚያካትት፣ በዘመናት መካከል የተገኘ አጋጣሚ ካለፈ እና ካመለጠ ዳግም ለማግኘት ብዙ ጊዜ እና መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነው፣ ይሄን ለማሳካት ደግሞ ሁሉም አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ነው ያሉት።
የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ አሳትፎ የሀገር ችግር እንደማይፈታ ከዚህ በፊት ያለ ተሞክሮ ነው ያሉት ቃል አቃባዩ የሚጨበጥ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ሁሉንም አካታች ማድረግ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የትኛውንም አካል የማሳተፍ ኀላፊነት አለበት፣ ሁሉንም ያሳትፋል ነው ያሉት። በሀገሬ ላይ ያገባኛል የሚል ሁሉ መሳተፍ አለበት፣ ኮሚሽኑም አጀንዳ አለኝ የሚልን አካል ሁሉ ያሳትፋል ነው ያሉት።
የሀገርን እንድነት ለማጽናት፣ ሰላምን ለማወጅ፣ ሀገርንም ለማሳደግ መመካከር እና መወያየት የተገባ ነው። በውይይት ሀገር ይጸናል። በውይይቱ መሰናክል ሁሉ ይታለፋልና።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
