
ደሴ: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የውሳኔ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል። አሚኮ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች በኮምቦልቻ ከተማ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዲጠናከር የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ወጣት ነኢማ ዳውድ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ ከቤተሰብ ጀምሮ ለሰላም መስፈን ልዩ ልዩ ሥራዎችን ማከናወናቸውን ገልጻለች፡፡ ብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው ትኩረት ከሰጣቸው አንኳር ጉዳዮች ውስጥም ከነጠላ ትርክት ይልቅ ገዢ ትርክት እንዲሰፍን ወጣቱ ትኩረት እንዲያደርግ መኾኑን አንስታለች።
ሌላኛው ወጣት ሲራጅ ዓሊ ወጣቶች ለሀገር ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ገልጿል። ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን ኀላፊነት እየተወጡ መኾናቸውን ጠቅሷል፡፡ ወጣቶች አሁን የተፈጠረላቸውን የቴክኖሎጂ አብዮት ተጠቅመው ራሳቸውን እና ሀገራቸውን ለማበልጸግ እንዲጠቀሙበትም አሳስቧል፡፡
በፓርቲው የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ለተሻለ ልማት እንደሚተጉም ተናግረዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ አቢ ወጣቶች የሀገርን ሁሉን አቀፍ ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ወጣቱ ትውልድ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በሚያደርገው ንቁ ተሳትፎ እና የጠራ አቋም ሀገር ትጸናለች ያሉት ኀላፊው ወጣቶች ፓርቲው ባስቀመጠው አቅጣጫ ተሳታፊ በመኾን የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። ወጣቶች የማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በማዋል እና አፍራሽ አመለካከትን በመመከት ሚዛናዊ ኾኖ ነገሮችን በማየት በልማት ጉዳይ ላይ የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
