
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዝናብ አጠር በመኾኑ በየጊዜው ድርቅ ይከሰትበታል። በዚህም ምክንያት በርካታ የአካባቢው ሕዝብ ለእርዳታ የተጋለጠ ነው። በአንጻሩ አካባቢው ዓመቱን ሙሉ የማያቋርጡ ወንዞች እና የከርሰ ምድር ውኃ ባለቤትም ነው። ይህን አካባቢ ታዲያ ካለበት ችግር ለማውጣት የመስኖ ልማት የሞት ሽረት ጉዳይ እንደኾነ ተወስዶ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
የሰቆጣ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር በየነ ተማረ ባለፉት ጊዜያት ባጋጠመው ድርቅ ሰለባ ነበሩ። አርሶ አደሩ ባለፉት ጊዜያት በተፈጠረው ድርቅ እጃቸውን ለእርዳታ ዘርግተውም ነበር። አርሶ አደሩ እንደሚሉት የሰው እጅ እና ፊት እሳት ነው ተቀብለኸውም ከጎን አይደርስ ሲሉ ሲወስዱ የነበረውን እርዳታ ምንያክል ያሸማቅቃቸው እንደነበር አስረድተዋል።
አርሶ አደሩ ከዚህ ችግር ለመውጣትም በቀያቸው ያለውን ወንዝ ጠልፎ መስኖ ማልማት የመኖር ያለመኖር ጉዳይ እንደኾነ አምነው ለመሥራት በመነሳታቸው ታሪካቸውን መቀየራቸውን ነግረውናል። አርሶ አደሩ አኹን ላይ በመስኖ ማሽላ፣ ገብስ፣ ስንዴ እና ጤፍ በዋናነት እንደሚያመርቱ ተናግረዋል። በዚህ ዓመትም ስንዴ፣ ጤፍ እና ማሽላ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የእርሻ መሬታቸውን ለሦስተኛ ጊዜ ማረሳቸውን እና የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በመጠቀም መሬታቸውን ዝግጁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ከሰባት እስከ ስምንት ጥማድ መሬት በዘር እንደሚሸፍኑ እና የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የሰብል ልማት ባለሙያ አበበ ሉሌ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የዝናብ አጠር በመኾኑ የመስኖ ልማት ሥራ የአካባቢው ማኅበረሰብ ዋስትና በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ባለሙያው በበጋ መስኖ ልማት ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ወረዳው ማሽላ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና ባቄላ በስፋት እንደሚያመርት እና ከ360 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝም ይጠበቃል ነው ያሉት። 15 ሺህ 937 ሄክታር መሬት በአንደኛ ዙር እርሻ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ መዋሉን የተናገሩት ባለሙያው ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በሁለተኛ ዙር እርሻ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
50 ሄክታር መሬት በዘመናዊ ትራክተር መታረሱን እና ቀሪው የሦስተኛ ዙር እርሻ እስከ ሰኔ 30 ድረስ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል። ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ 145 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ፍግ ወደ ማሳ መግባቱን እና 37 ሺህ ኪዩቢክ ሜትሪክ ኮምፖስት መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
1 ሺህ 300 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለወረዳው መቅረቡንም ገልጸዋል። የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መግዣ ዋጋ መወደድ በአርሶ አደሩ ዘንድ ቅሬታ ያስነሳ ቢኾንም ከዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ መኾኑን በማስረዳት መግባባት መፈጠሩን ተናግረዋል። የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መግዛት የማይችሉ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ ምክር እና ድጋፍ እየተሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ እንደየሰብል አይነቱ መሬቱን ደጋግሞ በማረስ ምርቱን ውጤታማ ለማድረግ የግብርና ባለሙያው እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። በዚሁ ሥራ ከ29 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ መኾናቸውንም ለአሚኮ ተናግረዋል። በ2017/18 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ በማቀድ እየሠራ መኾኑን የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ ተናግረዋል፡፡
መምሪያ ኀላፊው በአሥተዳደሩ የተለያዩ የአፈር ለምነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ማዳበሪያዎች ከመስከረም ወር ጀምሮ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት። 278 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ኮምፖስት መዘጋጀቱን እና የተብላላ ፍግ ወደ ማሳ መሰራጨቱንም ተናግረዋል። 2 ሺህ 450 ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት መዘጋጀቱን የተናገሩት ኀላፊው 51 ሺህ 995 ኩንታል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ግብዓት መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል፡፡
በአሥተዳደሩም 11 ሺህ 231 ኩንታል ለአርሶ አደሩም መሰራጨቱን ገልጸዋል። አካባቢው ዝናብ አጠር ከመኾኑ ጋር ተያይዞ በሚከሰተው ድርቅ ምክንያት አርሶ አደሩ እንደሚፈተን ያወሱት ኀላፊው አሁን በአካባቢው የሚገኙ ወንዞችን በመጥለፍ ከዓመት እስከ ዓመት ምርት በማምረት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በዚህም እስካሁን ባለው ከ620 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ መልማቱን ተናግረዋል፡፡ ከ428 ሺህ ኩንታል በላይ ፍራፍሬ ደግሞ ለገበያ ቀርቧል ብለዋል፡፡ ለአርሶ አደሩ 145 የውኃ መሳቢያ ፓንፖች ተሰራጭቷል ነው ያሉት፡፡
ይህ በመስኖ ልማት ሥራ የታየው በምግብ ዋስትና እራስን የማስቻል ጅምር የሥራ ውጤት ነው ያሉት ኀላፊው ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል የክልሉ መንግሥትም ኾነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊ ግብዓቶችን በመደገፍ ርብርብ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው ለአሚኮ እንዳሉት በክልሉ ለ2017 የምርት ዘመን 43 ሺህ 151 በአዲስ እና 299 ሺህ 329 ሄክታር መሬት በነባር መስኖ ለማልማት በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ መጋቢት መጨረሻ አካባቢ የመስኖ የሁለተኛ ዙር ሽፋንን ከፍ በማድረግ ብዙ ምርቶችን ወደ ገበያ ለማስገባት ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
