የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።

16

ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ለኢትዮጵያዉያን ልዕልና” በሚል ሀሳብ ከአባላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው። ውይይቱ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ የታዩ ለውጦች እና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ያተኮረ ነው።

የውይይቱ ተሳታፊ ዘላለም ታከለ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ብሎም በክልሉ የተሠሩ እና እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ የሚፈቱ ናቸው። የሚሠሩ ሥራዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ደግሞ ለሠላም ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል።

የሚነሱ ችግሮችን በውይይት መፍታት እና ለሕዝብ ጥያቄዎችም ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል። ተሳታፊው መንግሥት የተቋማትን የአገልግሎት አሠጣጥ በመፈተሽ ችግር ያለባቸውን አካላት ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም ነው የገለጹት። ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ ውድነሽ ተመስገን በከተማ አሥተዳደሩ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ለነዋሪዎች ብሎም ለጎብኝዎች ተመራጭ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጅ አኹንም መንግሥት የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ እና የተቋማትን የአገልግሎት አሠጣጥ ማሻሻል ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ እንዳሉት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ለኑሮ ውድነት፣ ሕገ ወጥነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲባባሱ አድርጓል።

በክልሉ ብሎም በከተማ አሥተዳደሩ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ ውይይቶች ተደርገዋል፤ በመንግሥት በኩልም በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ተደርጎ በርካታ የታጠቁ ዜጎች ተሃድሶ ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ገልጸዋል። በክልል ደረጃ የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ ችግሩን በድርድር ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለቅረፍም የእሑድ የግብይት ቦታዎችን የማቋቋም እና የመጀመሪያ ደረጃ የገበያ ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። በተቋማት የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ እየተሠራ ይገኛል። የዲጅታል አሠራርም ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑን ነው የገለጹት።

በከተማ አሥተዳደሩ ብሎም በክልሉ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ማኅበረሰቡ አጋዥ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኩራታችን የኾነው የሕዳሴ ግድብ የመጨረሻችን መኾን የለበትም።
Next article“የመስኖ ሥራ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ነው” አርሶ አደር