
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ሕዝቦቿን ከጨለማ ለማውጣት እና ምጣኔ ሃብቷን ለማሳደግ በአፍሪካ ግዙፍን የሕዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። እነኾ የዐይን ማረፊያ የኾነው የዐባይ ግድብም ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፍ ደርሷል። ውጥኑ እንዳይሳካ ብዙዎች ሴራ የሸረቡበት ሕዳሴ ግድብ እነኾ አሁን ላይ ለሚሳሱለት ኢትዮጵያውያንም እሸት ማቅመስ ጀምሯል። የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እና የዓሳ ምርት ጅማሮ ከሰጠባቸው በረከቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
የውኃ ሀብት ተደራዳሪው ፈቅ አሕመድ የሕዳሴ ግድቡ እዚህ የደረሰው አልጋ በአልጋ በኾነ መንገድ እንዳልነበር ትውስታቸውን ገልጸዋል። በተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ከግብጽ እና ሱዳን ገጥሞት የነበረው ፈተና ሊዘነጋ የማይገባው ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በሆደ ሰፊነት እና በጽኑ የሀገር ፍቅር ስሜት ፈተናውን አልፈው እዚህ እንዲደርስ አድርገውታል ነው ያሉት።
ግብጽ የግድቡን ጉዳይ ዓለም አቀፍ የክርክር አጀንዳ ለማድረግ ብትሞክርም እንኳ የመጡትን ጫናዎች ሁሉ በብልጠት እና በጀግንነት መወጣት የተቻለ መኾኑንም አውስተዋል። ግብጾች ከውይይት እና ክርክር ባለፈ ወደ ማስፈራራት ሁሉ ገብተው የነበር ያሉት ተደራዳሪው ጉዳያቸውን በብስለት ከንቱ ኾኖ እንዲቀር ማድረግ እንደተቻለም ተናግረዋል። በፈተናዎች ታጥሮ የነበረው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተከፈለው ዋጋ ሁሉ ተከፍሎ በጽናት እዚህ ደርሷል ነው ያሉት።
ዓባይ ሲነሳ አብረው የሚነሱት በ1929 ዓ.ም በብርታኒያ እና በግብጽ መካከል የተደረገው በስህተት የታጀበው እና ኢትዮጵያን ያገለለው ስምምነት፣ በ1959 ዓ.ም የተደረገው የግብጽ እና የሱዳን ስምምነት የውኃ ዲኘሎማሲያችን ላይ የነበራቸው ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ እነዚህን ስምምነቶች ባለመቀበሏ እና በሌለችበት የተከወኑ ናቸው የሚለው እውነታን ያዘለው የመከራከሪያ ነጥብ ፍሬያማ እንደነበርም ያወሳሉ። አሁን ላይ ከረጅም ዓመት ድርድር በኋላ የናይል ተፍሰስ የትብብር ማዕቀፍ የሚባለው የሕግ ማዕቀፍ እንዲጸድቅ የተደረገበት ሁኔታም ሌላው ስኬት ነው ይላሉ። የሕግ ማዕቀፍም እንዲጸድቅ ከ15 ዓመት በላይ ትግል እንደተደረገበትም አውስተዋል። ስምምነቱን ያጸደቁ ሀገራትም ከዚህ በኋላ የሚተዳደሩት በቅርብ በጸደቀው ሕግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የውኃ ማማ ናት ሲባል ውኃን ከከፍታ ቦታ ወደታች የምትለቅ ሀገር ናት ለማለት እንጂ የውኃ ሀብታም ናት ማለት አይደለም የሚሉት ተደራዳሪው ያለንን ሀብት በተገቢው መንገድ መጠቀም እና ማልማት አለብን ይላሉ። እንደ ሀገር ያለን ሀብት መሬት እና ውኃችን በመኾኑ ጎረቤት ሀገሮች በማይጎዱበት መንገድ ተጠቃሚነታችንን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።
አሁንም ቢኾን የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ላይ ደርሷል ብለን እጅ እና እግራችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም ይላሉ። በቀጣይም የውኃ አጠቃቀም እና አለቃቀቅ ላይ ሥራዎች ይጠበቁብናል ብለዋል። ከቀጣናዊ ሀገሮች ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነትም ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ግድቡ አሁን ላይ በተለይ የግንባታ ሥራው ተጠናቅቋል ማለት ይቻላል፤ የሚቀረው ተርባይኖችን አጠናቅቆ የማስገባት እና ኃይል እንዲያመነጩ የማድረግ ሥራዎችን መጨረስ እና ቀሪ ተግባራትን ማጠናቀቅ ይኾናል ብለዋል።
ግድቡ በዘገየ ቁጥር ሀገር ማግኘት ያለባትን ጥቅም አታገኝም ያሉት ተደራዳሪው ለቀሪ ተግባራት ትኩረት መስጠት እና መጠናቀቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በሀገራችን ሀብት እና አቅም እዚህ የደረሰው እና ኩራታችን የኾነው የሕዳሴ ግድብ የመጨረሻ መኾን የለበትም ብለዋል። ሌሎች ላይም ሊታሰብ እንደሚገባም ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያን ግድቡ እዚህ እንዲደርስ ያደረጉት ድጋፍ ከገንዘብ ባሻገር ነው ብለዋል። በቀጣይም በእንዲህ አይነት ሀገራዊ ተግባር ላይ የመረባረብ ባሕሉ ሊጠናከር እንደሚገባውም አንስተዋል። ያ ሲኾን በሕዝቦች ዘንድም ብሔረዊ አንድነት የሚባለው ነገር በተግባር ይኾናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
