
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በአሲድ የተጠቃ የእርሻ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ዋለ መርሻ አሲዳማ የእርሻ መሬትን በኖራ የማከም ሥራ በንቅናቄ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም 5 ሺህ ኩንታል ኖራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመው አሁን የተጀመረው ፍኖተ ካርታም በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል። በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ግብ ተጥሎ እየተሠራ መኾኑም ተመልክቷል።
የቢሮው ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት ፍኖተ ካርታው በአሲዳማነት የተጠቁ የእርሻ መሬቶችን ስፋት፣ የጉዳት መጠን እና የሚያስፈልገው የኖራ ብዛትን በጥናት በመለየት መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ነው። በክልሉ የአሲዳማነት ችግር ጎልቶ የሚታይ ነው ያሉት አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው ይሄን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ጥናቱም የባሰ ችግር ያለባቸውን ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በማካተት ምን ያህል ሄክታር መሬት በምን ያህል ስፋት እንደተጠቃ በከፍተኛ፣ በመካከለኛ እና በዝቅተኛ ደረጃ የሚያስቀምጥ መኾኑን ገልጸዋል። በሚካሄደው ጥናት ላይም አርሶ አደሮች ለሙከራ ሰርቶ ማሳያ የሚኾኑ መሬቶችን በማዘጋጀት የሚገኘውን ተሞክሮ በመቀመር እና በማስፋት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት 200 ሺህ ኩንታል የኖራ አፈር በመግዛት 12 ሺህ 360 ሄክታር በአሲድ የተጠቃ መሬትን ለማከም እየተሠራ እንደሚገኝም የግብርና ቢሮውን መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
