ተቋርጦ የነበረው የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ 53 በመቶ መድረሱ ተገለጸ፡፡

59

ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለማከናወን በእቅድ ከያዛቸው ከተሞች መካከል አንዷ ዕድሜ ጠገቧ የደብረ ማርቆስ ከተማ ናት፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ በግማሽ ቢሊዮን ብር ወጭ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ ላይ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ተናግረዋል፡፡

ቀደምት በሀገሪቱ የአውሮፕላን ትራንስፖት ተጠቃሚ ከነበሩ ግንባር ቀደም ከተሞች መካከል ደብረ ማርቆስ አንዷ ናት፡፡ ነገር ግን በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ነባሩ አውሮፕላን ማረፊያ መዘጋቱ ለዘመናት ነዋሪዎችን ቁጭት ውስጥ ያስገባ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት በኅብረተሰቡ ዘንድ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።

አቶ ሙሉዓባይ ታምሩ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ የተጀመረው የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የደብረ ማርቆስ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ነበር ይላሉ፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክቱ መጀመሩ ያስደሰታቸው መኾኑን የገለጹት ነዋሪው በፍጥነት ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ጥያቄ አንስተዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ተጨማሪ የትራንስፖርት አማራጭ ኾኖ ያገለግላል ብለዋል፡፡ የደብረ ማርቆስ ከተማ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በተያዘ በጀት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሠራ የፌዴራል ፕሮጀክት መኾኑን የተናገሩት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ በ931 የሥራ ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀድም በታሰበለት ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም ብለዋል ከንቲባው፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡት የወሰን ማስከበር ችግሮች፣ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ የአየር ንብረቱ ምቹ ያለመኾን እና በመሠረታዊነት የጸጥታ ችግሩ መፈጠር የከተማዋ ከንቲባ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ተቋርጦ የነበረው ፕሮጀክት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ እንደ ተጀመረ የተናገሩት ከንቲባው ተቋርጦ የነበረበትን ጊዜ ለማካካስ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት እና የትርፍ ሰዓት ሥራን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ከነበረበት 37 በመቶ ወደ 53 በመቶ አፈጻጸሙን ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ይህ ፕሮጀክት አሁን ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በ2018 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል አመራሮች፣ የከተማ አሥተዳደሩ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአማራ ክልል የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራዎች ላይ ሁሉም በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ።
Next articleየፍታብሔር እና የወንጀል ሕግ አንድነት እና ልዩነት፦