
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ የጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ በባሕር ዳር ይካሄዳል። የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራው ለቀናት ይቆያል ነው የተባለው። የክልሉ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላም በክልሉ ተጨማሪ አጀንዳዎች ከመጡ የመሠብሠብ ሥራው ቀጣይነት ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ወሳኝ፣ መሠረታዊ እና ሀገራዊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ አለመግባባቶችን እና ልዩነቶችን በመለየት አጀንዳ በመቅረጽ ምክክር እንዲደረግባቸው የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ደግሞ በአግባቡ ተግባራዊ ኾነው በሀገር ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ ማስቻል ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ በክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ላይ ሥራዎችን ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከዕቅዱ አንጻር ጥቂት መዘግየት ታይቷል ያሉት ቃል አቀባዩ ከመጭው ቅዳሜ ጀምሮ የክልሉን አጀንዳ የማሠባሠብ፣ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን የሚወከሉ ሰዎችን የመምረጥ ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል።
በአማራ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ላይ ሥራ ሢሠሩ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል። የተሳታፊ ልየታ መደረጉንም ገልጸዋል። በወረዳዎች እና በከተማ አሥተዳደሮች ላይ የተለዩ ተሳታፊዎች ከቅዳሜ ጀምሮ በሚደረገው የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ይሳተፋሉ ነው ያሉት።
በባሕር ዳር የሚደረገው የክልሉ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራው በትኩረት እንደሚሠራበትም ገልጸዋል። የክልሉ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ከቅዳሜ ጀምሮ ለቀናት እንደሚቆይም ተመላክቷል። ኅብረተሰቡ የእስካሁን ሥራው የተሳካ እንዲኾን ያደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በአጅንዳ ማሠባሠብ ሥራው በአማራ ክልል ያገባኛል የሚሉ አካላት ሁሉ ይሳተፋሉ ነው የተባለው። በአማራ ክልል በኩል በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሊነሱ እና ሊታዩ ይገባቸዋል የተባሉ አጀንዳዎች ይለያሉም ነው ያሉት። የአማራ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮችም ይመረጣሉ ነው የተባለው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራው ሠፊ እና አሳታፊ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ሥራው ስኬታማ እንዲኾን የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል። ኮሚሽኑ ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ ከባላድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል የሚኖረው የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ስኬታማ እንዲኾን ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል። የአማራ ክልልም ኾነ ሀገር እንደ ሀገር ከችግር እንድትወጣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡን የወከሉ ተወካዮች አጀንዳቸውን ይዘው በንቃት መሳተፍ አለባቸው ብለዋል። ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም በንቃት መሳተፍ አለባቸው ነው የተባለው። የአማራ ክልል በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚወከልባቸው አጀንዳዎችን ለመሠብሠብ የሚያስችል ንቁ ተሳትፎ እና ትብብር ይጠበቃል ተብሏል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳታፊነት እና አካታችነትን መርህ አድርጎ እንደሚሠራም ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ተሞክሮ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሟላ ሰላም ባለበት ሁኔታ ብቻ ላይካሄድ ይችላል ያሉት ቃል አቀባዩ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንደኛው የመፍትሔ ሃሳብ ስለሚኾን በግጭት ውስጥም ሊካሄድ ይችላል ነው ያሉት። ያ ማለት ግን በፍጹም ግጭት ውስጥ ይካሄዳል ማለት አይደለም ብለዋል።
በአማራ ክልል አጀንዳ ማሠባሠብ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል። የአጀንዳ አሠባሠብ ሥራው አካታችነቱን እና አሳታፊነቱን ጠብቆ እንደሚካሄድም ገልጸዋል። በክልሉ ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ጥሪ እንደተደረገላቸውም አንስተዋል።
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት ሁሉ መሳተፍ እንደሚችሉም ገልጸዋል። በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሠባሠቡ በባሕር ዳር ከተካሄደ በኋላም ተጨማሪ አጀንዳዎች ካሉ የአጀንዳ ማሠባሠቡ ሥራ ይቀጥላል ነው ያሉት። የክልሉ አጀንዳ ተሠበሠበ ተብሎ የሚዘጋ በር የለም ብለዋል። አካታችነቱ እና አሳታፊነቱ የተሻለ ኾኖ እንዲቀጥልም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!