
ደብረብርሃን፡ መጋቢት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ያሠለጠናቸው የ33ኛ ዙር የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት በደብረ ብርሃን ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በአቀባበል መርሐ ግብሩ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሐግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት ሰላም እና ልማት ወዳዱን ማኅበረሰብ ስለተቀላቀላችሁ ደስ ብሎናል ብለዋል።
የአማራ ክልል የሰላም እጦት ገጥሞታል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ይሄ ደግሞ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ወደኋላ የሚያስቀር በመኾኑ ሰላምን የማጽናት ሥራ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ የዞኑን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የጸጥታ መዋቅሩ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደኾነ አንስተዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፈታት አለባቸው ያሉት አሥተዳዳሪው ከዚህ በተቃራኒው የኾነ አካሄድ ግን ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።
በቀጣይ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ የዞኑ አሥተዳደር ለጸጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።
የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላትም በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። ቀጣይ ተልዕኮን በብቃት ለመወጣት ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!