የአድማ መከላከል አባላት በደባርቅ ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው።

65

ደባርቅ፡ መጋቢት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን በብርሸለቆ ያሠለጠናቸው የ33ኛ ዙር ተመራቂ አድማ መከላከል ፖሊስ አባላት በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በአቀባበል መርሐ ግብሩ የሰሜን ጎንደር ዞን እና የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች ተገኝተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ በመከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ መዋቅር አባላት፣ በፖለቲካ መሪዎች እና በማኅበረሰቡ የጋራ ጥረት በዞኑ በሚገኙ አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም እንዳለ ተናግረዋል።

የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላትም የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል። በወሰዱት ንድፈሃሳባዊ እና ተግባራዊ ሥልጠና ታግዘው ተልዕኳቸውን ሊያሳኩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላልኝ አምሳሉ ተመራቂ የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላቱ የተጀመሩ የልማት እና የመልከም አሥተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሰላም እና ደኅንነትን በማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የ3ኛ ሻለቃ 6ኛ ሻምበል አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ከፍያለው አቡሃይ ቃል የገቡበትን በማስጠበቅ እና ሕዝባዊ ወገንተኝነትን በመላበስ የቀደመ የሠራዊቱን መልካም ስም እና ታሪክ ማስቀጠል አለባቸው ብለዋል።

አባላቱ ሥልጠናቸውን በአግባቡ ተከታትለው እና በከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ መነቃቃት ውስጥ ኾነው እንደመጡ ተናግረዋል። ተመራቂ የአድማ መከላከል አባላትም የተጣለባቸውን ሕገ መንግሥታዊ እና ሀገራዊ ኀላፊነት በመወጣት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አጋዥ እንደሚኾኑ ገልጸዋል።

ሕዝባዊ ወገንተኝነትን በመላበስ የሠራዊቱን መርህ በመከተል ማኅበረሰቡን እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል። በቀጣይም የጸጥታ መዋቅሩ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ማኅበረሰቡ አጋዥነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግሎባል የጥቁር ሕዝቦች ማዕከልና እና ዩኔስኮ የመግባቢያ ስምምነት ለማዘጋጀት እና ለመፈረም ተስማሙ።
Next articleየአድማ መከላከል አባላት በደብረብርሃን ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው።