
ባሕርዳር: መጋቢት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ማዕከልና እና በዩኔስኮ መካከል ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱን ያካሄዱት የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ደመቀ መኮንን ከዩኔስኮ የአፍሪካ እና የውጭ ግንኙነት ረዳት ዋና ዳይሬክተር ፌርሜን ኡድዋርድ እና ከዩኔስኮ ዓለምአቀፍ የቅርስ ዳይሬክተር ላዛሬ ኢሉዋንዱ ጋር ነው። ውይይቱ በዩኔስኮ ዋና መሥሪያ ቤት በፓሪስ ነው የተካሄደው።
የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ደመቀ መኮንን የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ማዕከልን ተልእኮዎች እና ዓላማዎችን በዝርዝር አስረድተዋል።
በትምህርት፣ ባሕል፣ ቅርስ እና የጋራ መርሐ ግብሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ትብብርን ለማጎልበት ስልቶችን ማዘጋጀት ያለው ጠቀሜታ ትኩረት ተሰጥቶበታል።
ሁለቱም የዩኔስኮ የሥራ ኀላፊዎች በማዕከሉ ዙሪያ ላይ የተደረገውን አጠቃላይ መግለጫ አድንቀዋል። በተለይም በባሕል፣ በቅርስ እና ትምህርት ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ያላቸውን ዝግጅነት ገልጸዋል።
በሁለቱም ማዕከላት ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎች ተጨማሪ ውይይቶችን በማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ለማዘጋጀት እና ለመፈረም ተስማምተዋል።
ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ግሎባል የጥቁር ሕዝቦች ማዕከል፣ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ዓለም አቀፍ የሲቨክ ድርጅት ሲኾን በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ እና ትምህርት ዙሪያ ትኩረት አድርጎ ይሠራል።
እ.ኤ. አ በታኅሳስ 8 / 2023 የተቋቋመው ማዕከሉ ዋና መሥሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!