ከ295 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

50

እንጅባራ: መጋቢት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር 856 ሺህ 660 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው ለ2017/18 የምርት ዘመን 407 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል። ከዚህም 17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ነው ያሉት።

ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ 856 ሺህ 660 ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ወደ ማዕከላት 295 ሺህ 647 ኩንታል ማዳበሪያ መግባቱን ገልጸዋል።

ከቀረበው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ደግሞ 62 በመቶ የሚኾነው ወደ መሠረታዊ ማኅበር ተጓጉዟል ነው ያሉት። 51 ሺህ 577 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን አስታውቀዋል።

ግብርና መምሪያው ከአድማስ ዩኒዬን ጋር በመቀናጀት የምርጥ ዘር፣ ሰው ሠራሽ የአፈር ማደበሪያ እና ሌሎች ለምርታማነት የሚያግዙ ግበዓቶችን በማቅረብ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ዩኔዬኑም የግብርና ግብዓቶችን በስፋት እያቀረበ መኾኑን ገልጸዋል። የግብዓት አሥተባባሪ ኮሚቴውም በየጊዜው አቅርቦቱን እና ሌሎችን የግብርና ልማት ተግባራት በመገምገም እየመራ መኾኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ጭማሪ መኖሩን የጠቆሙት ምክትል ኀላፊው ይህ የኾነው የዶላር ፣የነዳጅ እና የትራንስፖርት ጭማሪ ጋር ተያይዞ መኾኑን ገልጸዋል።

ስለ ዋጋ ጭማሪው ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ምርታማነትን በዘላቂነት ለማስቀጠል ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ይልቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) መጠቀም ወሳኝ በመኾኑ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ኮምፖስት የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት። 97 በመቶ የሚኾነው መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

በአድማስ ዩኒዬን ግብዓት አቅርቦት ስርጭት እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት ክፍል ኀላፊ ምኒሻ ቢተው በሁሉም ማዕከላት መካዘኖችን ንጹሕ በማድረግ ማዳበሪያ እያስገቡ እንደኾነ ገልጸዋል።

የቀረበውን ማደበሪያ ወደ መሠረታዊ ማኅበራት እየተሠራጨ ነው ያሉት ኀላፊው ከዩኒዬኑ መካዘኖች በተጨማሪ አምስት የግል መካዘኖችን በመከራየት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ወደ መሠረታዊ ማኅበራት የገባው የአፈር ማደበሪያ ለአርሶ አደሮች በአፋጣኝ መሰራጨት አለበትም ብለዋል።

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የሚቀርቡ የግብርና ግብዓቶች ክትትል ባለሙያ አታላይ ወርቅነህ ወደ መሠረታዊ ማኅበራት የቀረበው ሰው ሠራሽ ማደበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሠራጨ መኾኑን ተናግረዋል።

የጸጥታ ችግር ያለባቸው ወረዳዎች ላይ ግብዓት በወረዳ ማዕከላት መካዘን ተከራይተው እንዲያሰራጩ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ: ሰለሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተፋሰስ ልማት በአማራ ክልል
Next articleግሎባል የጥቁር ሕዝቦች ማዕከልና እና ዩኔስኮ የመግባቢያ ስምምነት ለማዘጋጀት እና ለመፈረም ተስማሙ።