‘‘ብዙ እየተወራለት ትንሽ ኢንቨስት የሚደረግለት ዘርፍ መሆን የለበትም፡፡’’ ዶክተር ክንዴ ተስፋዬ

210

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ የግብርና ልማት የዘመናት ሂደት እና ደረጃ ከትናንት መሻል ቢያሳይም ከሕዝብ ቁጥር መጨመር አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አለማሳየቱን በዓለም አቀፍ የበቆሎና የስንዴ ምርምር ከፍተኛ ተመራማሪ ክንዴ ተስፋዬ (ዶክተር) ተናገሩ፡፡

የግብርናውን ዘርፍ በውጭ ሀገር በሚመጣ የአፈር ማዳበሪያ እና ማሽነሪዎች በዘላቂነት ማሳደግ እንደማቻልም ዶክተር ክንዴ ይሞግታሉ፡፡ ‘‘የግብርና አዳዲስ የሥርጸት ተግባራትን መቀበል የሚስችል የአርሶ አደር ሽግግር አለመፍጠር፤ መሰል የአየር ንብረት ካላቸው ሀገራት ጋር የሚሠሩ ልምዶችን አለመተግበርና በትንንሽ የአርሶ አደር ማሳዎች ኢንቨስት አድርጎ ማዘመን አለመቻል በኢትዮጵያ በክፍለ ዘመናት የግብርና ሂደት ሕዝቡን ሙሉ በሙሉ በምግብ ራሱን እንዳይችል አድርጓል’’ ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስትከተል የቆየች ቢሆንም እስካሁን ለዘርፉ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ገቢ 10 ከመቶ በታች ነው ኢንቨስት የምታደርገው፡፡ ‘‘በዚህ አግባብ ስለግብርናው ብዙ ከማውራት ውጭ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና የሕይወት መሠረታዊ ጥቅም መመለስ አይቻልም’’ ነው ያሉት፡፡

ዶክተር ክንዴ ከሁለት ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ባጠኑት ጥናት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የሚያገኙት የምርት መጠን ማግኘት ካለባቸው 30 በመቶውን ብቻ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ባለፉት 15 እና 20 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ የምግብ ፍላጎትም ጨምሯል፡፡ አሁን ባለው የምርታማነት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሁኔታ የሚጓዝ ከሆነ ኢትዮጵያ ከ20 እና 30 ዓመታት በኋላ ለከፍተኛ የምግብ አቅርቦት እጥረት እንደምተጋለጥ ስጋት መኖሩን አመላክተዋል፡፡
‘‘ስለዚህ ምን ይደረግ?’’ ለሚለው ዶክተር ክንዴ ሲመልሱ ‘‘ከውጭ ሀገራት የአፈር ማዳበሪያ እና ከዘር እስከ ጎተራ የሚከውኑ የማሽነሪዎች አሠራር ሐሳብ እንጂ ምርቶችን ማምጣት አይበጅም’’ ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ በምርምርና ጥናት የተረጋገጡ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም፤ ሀገር በቀል የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስፋፋት፤ የግብርና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረትና ለገበሬው በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ፤ የግብርና ሥርጸቱንም ለማሻሻልና ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ይገባዋልም ብለዋል፡፡

ገበሬው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የመጣ የአፈር ማዳበሪያ እንዲገዛ መደረጉ በምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድረበትም ያነሳሉ፡፡ የአፈር ማዳበሪያው የተሠራበት ጊዜ፣ ተስማሚነት እና የጥራት ጉዳዮች ፈታኝ ይሆኑበታል፤ በመሆኑም በአቅራቢያው በሀገር ውስጥ የአፈር ማዳበሪያ ምርቶች ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በምርጥ ዘር አጠቃቀም በኩልም የአምናን ምርጥ ዘር በማስቀመጥ መጠቀም ሳይሆን የምርጥ ዘር አቅራቢ ማኅበራት ወይም ዩኒየኖች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲያቀርቡ መሥራትና መከታተል እንደሚያስፈልግ ተመራማሪው አስታውቀዋል፡፡ ክረምቱን ሙሉ ከማረስ፣ ለቀናትም ከማጨድ በአጭር ጊዜ እና በጥራት እስከጎተራ የሚያደርሱ እንደየአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ማሽነሪዎችን የቴክኖሎጂ ምሩቃን እንዲሠሩት ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም ከሕንድ፣ ከባንግላዲሽ እና ጃፓንን ከመሰሉ ሀገራት መማር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
‘‘ኢትዮጵያ በግብርና ሥርፀት አርሶ አደሮችን ከአዳዲስ የግብርና አሠራሮች እና ግኝቶች ጋር በማስተዋወቅ እና ተደራሽ በማድረግ የዘረጋችው ተግባር ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል’’ ያሉት ዶክተር ክንዴ በተግባር ግን የግብርና ባለሙያዎች ምርምሩን ወደ ገበሬዎች ከማድረስ ይልቅ ከገበሬው የቆየ ባሕላዊ አሠራር ጋር ተጣብቀው የመቅረት ችግርን መቅረፍ ላይ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአርሶ አደር ሠርቶ ማሳያዎች አተገባበርን ተግባራዊ ማድረግ፤ አርሶ አደሩ መሬቱን የማልማት ግዴታውን በመጠቀም የቴክኖሎጂ አተገባበሩን በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆን መገምገም ይገባልም ብለዋል፡፡
በዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከዚህ በፊት በነበረ የሕይወት ልምድ ከዝናብ በፊት ቀድሞ በመዝራት ለችግር የመጋለጥ ሁኔታዎች ይስተዋላል፤ ይህንን ለመቀነስም አሁን በጅምር ላይ ያለውን ዲጅታል የአየር ንብረትና የግብርና መረጃ በተለይም ዝናብ የሚጀምርበትንና የሚቆምባቸውን ቀናት አርሶ አደሮች ቀድመው እንዲያውቁ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ በየሰፍራው ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በሕዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት በመሬት እጥረት የተራቆቱ ተራራዎችንና የተበጣጠሱ መሬቶችን ለሰብል ሥራ የሚያውሉ አርሶ አደሮች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከሰብል ከሚያገኙት ምርት ይልቅ ወደ ደን ልማት እና ጥብቅ ቦታዎች በመቀየር በማር ምርትና በእንስሳት መኖ አቅርቦት ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ መሥራት ላይ እንዲተኮርም መክረዋል፡፡

የሀገሪቱን የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ መሠረት በማድረግ እያንዳንዱ መሬት የሚለማው ለመኖሪያ፣ ለእርሻ፣ ለደን ወይስ ለአምራች ኢንዱስትሪ ተብሎ ተጠንቶ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ‘‘በኢትዮጵያ ግብርናው ብዙ እየተወራለት ትንሽ ኢንቨስት የሚደረግለት ዘርፍ መሆን የለበትም’’ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ክንዴ ለዚህ መፍትሔው በእጅ ከሌለው ዝናብ ይልቅ የመስኖና የጎሮ ልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት መሆኑን መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንዞችን ሁል ጊዜ ‘‘የተራጨንብሽ’’ ከሚሉ የዘፈን ማድመቂያትና የደንበር ምልክትነት አልፈው የሕይወት መሠረት መሆን እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡ የመስከረምን በረከት ተከትለው ‘‘ጋራ ሸንተረሩ፤ አበባው ማመሩ’’ እየተባሉ በጋ የሚራቆቱት ገመናዎቻችን የኑሮ ዑደታችን ሐቆች ናቸው፡፡ ለተራሮች አካባቢ የልምላሜ ትንሳኤ የግብርና ባለሙያዎችና የየአካባቢው ነዋሪዎች ብርቱ ጥረትን ቀጣይ የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዮቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous article“እኛ ስለእናንተ ማኅበራዊ ሕይወታችንን ረስተን እና ቤተሰቦቻችን ተለይተን በዚህ እንቆያለን፤ እናንተ ደግሞ ስለእኛ በቤታችሁ ቆዩ፡፡” ነርሶች
Next articleሰማይ ጠቀሱን ፎቅ ለፆመኞች ስንቅ