ኅብረተሰቡ የሚሰራጩ መረጃዎችን በአግባቡ እንዲመረምር አቶ ዛዲግ አብርሃ አሳሰቡ።

55

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ እና ሌሎች አማራጮች የሚሰራጩ መረጃዎችን ከመቀበሉ በፊት በአግባቡ መመርመር እንዳለበት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዛዲግ አብርሃ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን በብርቱካን ተመስገን ዙሪያ የተሠራውን የተቀነባበረ የሃሰት ዘገባ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ያለንበት ወቅት ዕውነት የተፈተነበት ነው ብለዋል። ውሸት ሀገርን እና ትልልቅ ሥልጣኔዎችን እንደሚያፈርስም ጠቁመዋል።

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ በዕውነት ላይ ትልቅ አደጋ መደቀኑንም ተናግረዋል። ማኅበራዊ ሚዲያ “በሁለት ጎን የተሳለ ቢላ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ በአግባቡ እና በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከሰሞኑ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በተደራጀ መልኩ የተሰራጨውን ሃሰተኛ መረጃ ለችግሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ድርጊቱ የብዙ ነገር ምልክት እና በርካታ ፍላጎት ያላቸው አካላት የመሩት መኾኑን በማንሳት ጉዳዩ መንግሥት ሴቶችን ለማብቃት እያከናወነ ያለውን ሥራ ወደኋላ የሚመልስ ነው ብለዋል።

ከዚህም በላይ ሁከት እና ብጥብጥ በማስነሳት ማኅበረሰቡን ወደ እርስ በእርስ ግጭት ለማስገባት ያለመ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

አጀንዳውን ያዘጋጁ እና ያሰራጩ አካላትም ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ የሴቶችን ክብር የሚነካ እኩይ ተግባር መፈጸማቸውን ነው ያስረዱት።

ኢቢሲ እንደዘገበው ድርጊቱ በዕውነት ላይ የተቃጣ አደጋ መኾኑን ገልጸው ሁሉም ከዚህ ድርጊት ትምህርት መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአድማ መከላከል አባላት በኮኪት ከተማ አቀባባል ተደረገላቸው።
Next articleየተፋሰስ ልማት በአማራ ክልል