
ገንዳ ውኃ፡ መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በብርሸለቆ ያሠለጠናቸው የ33ኛው ዙር አድማ መከላከል አባላት በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ኮኪት ከተማ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በመርሐ ግብሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች፣ የዞኑ፣ የወረዳ፣ የከተማ የሥራ ኀላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ዋኘው ዓለሜ የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላቱ የገቡትን ቃል በመጠበቅ በዓላማቸው ጸንተው ሕዝብን ማገልገል ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሀገርን ፍቅር በልብ ሰንቆ ጠላትን በመመከት ለሕዝብ ሰላም ዘብ ኾኖ መቆም ይገባል ነው ያሉት።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት የተጣለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አባላቱ ከኅብረተሰቡ ጋር በመግባባት እና በመቀናጀት ሰላምን አጽንቶ ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የተሰጣቸውን ሥልጠና ወደ ተግባር በመቀየር የአካባቢውን ሰላም በማስፈን ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ለማኅበረሰቡ ደጀን በመኾን የማኅበረሰቡን ችግር ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የውስጥ ጠላቷን በማጽዳት የሀገራቸውን ዳር ደንበር እንደሚያስከብሩም የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት ተናግረዋል።
በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው ቀጣናውን ሰላም እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!