መልካም ሥራ እና መልካም ሥነ ምግባር የረመዳን መገለጫዎች ናቸው።

20

ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሼህ አብዱልጣሂር ዓሊ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ይተዳደራሉ። በርካቶች በቸርነታቸው እና በልግስናቸው “አባታችን” በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸዋል። ሼህ አብዱልጣሂር በተለይ በረመዳን ወር አስቀድመው እነማንን እንደሚረዱ ይጠይቃሉ። ጠይቀውም ያጣራሉ። ለማን ምን ቢረዱ ሕይዎቱን ይታደገዋል ብለው ይወስናሉ።

ሰጠሁ እና እረዳሁ ባይባልም በረመዳን የተቸገረን ከመርዳት ተቆጥቤ አላውቅም። ወሩን ምክንያት በማድረግ ለተመረጡ ተማሪዎች የመማሪያ ግብዓትም እንደሚሰጡ ተናግረዋል። በሼህ አብዱልጣሂር መኖሪያ ቤት በአጥሩ በኩል ሁለት የቧንቧ ውኃ አለ፤ ከእርሳቸው መኖሪያ ቤት በቅርብ ርቀት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚኖሩ ወገኖችም አሉ። እነዚህ ወገኖች አቅም ያላቸው የቀን ሥራ በመሥራት ይተዳደራሉ። አቅመ ደካሞች ደግሞ ለምነው ያድራሉ።

እነዚህ የተቸገሩ ወገኖቻችን በተለይ ሕጻናት እና ሴቶች የንጹህ ውኃ ፍለጋ ሲባዝኑ ይመለከታሉ ። እናም እርሳቸው እና ቤተሰባቸው ችግረኞችን በማየት ማለፍ አልፈለጉም። ይልቁንም የቤታቸውን ቧንቧ ወደ ውጭ በማውጣት በሥነ ሥርዓት እንዲጠቀሙበት አድርገዋል። ከ30 በላይ የችግረኞችን ሕይዎት መታደግም ችለዋል።

ሼሁ በዚህ የተቀደሰ ተግባር ብቻ አላበቁም፤ በተለይ በረመዳን ወር ቤተሰቦቸ በቅዱስ ቁርዓን ሕግ መሠረት የተቸገሩትን በመርዳት፣ በማብላት እና በማጠጣት ያሳልፍሉ ነው ያሉን። ሼህ አብዱልጣሂር ዒድ አልፈጥር ከተናጠል ይልቅ በአብሮነት ለአቅመ ደካሞች ፍስሐን እንዲያገኙ በማድረግ የሚከበር የማፍጠሪያ በዓላችን ነው ብለዋል።

በዒድ አልፈጥር ደስታቸውን የሚገልጹት አቅመ ደካሞችን በማገዝ እና በመንከባከብ፣ ዘመድን በመዘየር (በመጎብኘት) የታመሙትን በመጠየቅ እና ሰውን በማስደሰት እንድኾነ አጫውተውናል። ከረመዳን ወር ባሻገር ደግሞ ሰርክ ከክርስቲያን እህት ወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ማኅበራዊ መስተጋብር አለንም ብለዋል። በሰርጉ ደግሰን እንደሰታለን። የታመመን እንጠይቃለን፤ የሞተ እንቀብራለን። በአካባቢ የልማት ሥራዎች በትጋት እንሳተፋለን። ተሳስበን እየኖርን ነው ብለዋል።

ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢ በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው እንደመጡ የነገሩን የአራት ልጆች እናት ወይዘሮ ፈንታነሽ ብርሃኑ አብዱልጣሂርን የብዙኃኑ አባት ብለው እንደሚጠሯቸው ነግረውናል። እሳቸው ባይኖሩ ምኑ ይበጀን ነበር የሚሉት ወይዘሮዋ በየጊዜው መኮረኒ፣ ፊኖ ዱቄት፣ እና የምግብ ዘይት እንደሚለግሷቸውም ተናግረዋ። አልባሳት እና ብርድ ልብስ እንደሰጧቸውም ወይዘሮዋ አጫውተውናል።

በባሕር ዳር ከተማ የሰላም በር መስጅድ የዳዕዋ ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ከማል አደም አናህዊ (ዶ.ር) ሙስሊሙ ጾሙን ምክንያት በማድረግ ራሱን ከመልካም ሥነ ምግባሮች አለማምዶ እና ሠርቶ በሕይዎቱ ማስቀጠል ስለኾነ “ረመዳን እና መልካም ሥነ ምግባር ይተሳሰራሉ” ነው ያሉት። መልካም ሥራ እና መልካም ሥነ ምግባር የረመዳን መገለጫዎች ናቸው ብለዋል።

ሰውን በሰውነቱ እና የፈጣሪ ፍጡርነቱን አውቆ መርዳት፣ እዝነት፣ ርህራሄ፣ ፈጣሪን መፍራት፣ ሞት አለብኝ እና እጠየቃለሁ ብሎ መገንዘብ ከዘመኑ አለመረጋጋት እንደሚያድን እና ይህ ደግሞ በረመዳን የበለጠ እንደሚተገበር ገልጸዋል።

ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ረመዳን የሚጾመው አላህን ለመፍራት እና መልካም ሰው ለመኾን ነው ብለዋል። በጾሙ ምክንያት ሥነ ምግባርን እና መልካም ሥራዎችን ለመሥራት መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ፈጣሪ በሁሉም ነገር የፈጠረው እና ያዘዘው ርህራሄን፣ መተዛዘን እና መተጋገዝን ነው ብለዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዒድ አልፈጥር ፍቅር የተገለጠበት ታላቅ በዓል መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰዒድ ኢብራሂም ተናገሩ።
Next articleየሃይማኖት ተቋማትን ማጠናከር በሥነ ምግባር የተገራ ትውልድ ማፍራት የሚያስችል መኾኑ ተመላከተ።