ዒድ አልፈጥር ፍቅር የተገለጠበት ታላቅ በዓል መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰዒድ ኢብራሂም ተናገሩ።

16

ሁመራ: መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ ተከብሯል። በዓሉ የተከበረው በሁመራ ከተማ ታላቁ አጢቅ መስጊድ ነው።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰዒድ ኢብራሂም “በዓሉ ፍቅር እና መተሳሳብ የተገለጠበት ነው” ብለዋል።

እርስ በእርስ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት በጎ ተግባራት ሲከወኑበት የቆየው የረመዳን ጾም ተጠናቅቆ የርህራሄ ተምሳሌት የኾነው የዒድ አልፈጥር በዓል ዛሬ ሲከበር በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ አለው ብለዋል።

መላው ሕዋሳችን ሲጾምበት የቆየው፣ ያለው ለሌለው ያለውን ሲያጋራበት የሰነበተው ጾም መደምደሚያ ዒድ አል ፈጥር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዓሉን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመደጋገፍ ማሳለፍ ይገባናል ነው ያሉት።

የዞን አሥተዳደሩ ከለውጥ በፊት አይተነው የማናውቀውን ድጋፍ፣ ትብብር እና ፍቅር በመስጠት ጾሙን ጀምረን እስክናጠናቅቅ ድረስ ከጎናችን ነበር ብለዋል። እኛም የመንግሥትን ሰላም የማጽናት ተግባር ከልብ እንደግፋለን ነው ያሉት።

መላው ሕዝበ ሙስሊም የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ እና ከመላው ሕዝበ ክርስቲያን ጋር ያለውን ፍቅር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ረመዳን ቁራን የወረደበት ታላቅ ወር ነው ያሉት ደግሞ ሼህ አብዱሰላም ኢብራሂም ናቸው። ሕዝበ ሙስሊሙ በታላቅ ደስታ በዓሉን እያከበረ ነው ያሉት ሼህ አብዱሰላም ዒድ ማለት አዲስ ከመልበስ ባለፈ ለሰው ልጅ በመኖር የሚገለጽ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ሙስሊም ክርስቲያኑ ተዋዶ እና ተፋቅሮ የሚኖርባት ሀገር መኾኗንም ገልጸዋል። እኛም በየአካባቢያችን አንዳችን ለአንዳችን በመተሳሰብ በፍቅር መኖር ይገባናል ብለዋል።

የሃይማኖቱ ተከታይ ወጣቶችም ከረመዳን እስከ ዒድ አልፈጥር በበጎ ተግባራት ሲሳተፍ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

የጎዳና ላይ ኢፍጣርን በማስተባበር እና በማስተናገድ ወጣቶች ሚናቸውም ሲወጡ እንደነበር አንስተዋል። ሃይማኖት ሳይለየን ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር በፍቅር በጋራ ተሳትፈናል ነው ያሉት።

ሃይማኖታችን ጾም፣ ስግደት እና ሶላትን ያዝዛል ይሄንንም አድርገን ለታላቁ በዓል ደርሰናል ብለዋል። ሰላምን በመጠበቅ የሰው ልጅ ያለ ስጋት የሚኖርባት ሀገር እንድትኖር በመከባበር እና በመቻቻል አብሮ የመኖር እሴቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቅም ያጡትን በማሰብ መርዳት እና መደገፍ የሃይማኖቱ ግዴታ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸሪዓ ፍርድ ቤት ሠብሣቢ ሼህ ወለላው ሰይድ ገለጹ።
Next articleመልካም ሥራ እና መልካም ሥነ ምግባር የረመዳን መገለጫዎች ናቸው።