
ለሰው ማዘንን እና ለሰላም መትጋትን ማስቀደም እንደሚገባ የጎንደር ከተማ ዑለማ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሼህ ኢብራሂም ሙሐመድ ገለጹ። ጎንደር፡ መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 446ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በጎንደር ከተማ አጼ ፋሲለደስ ስቴዲየም ተከብሯል።
በበዓሉ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ እና ጥሪ የተደረገላቸው የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። የጎንደር ከተማ ዑለማ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሼህ ኢብራሂም ሙሐመድ በረመዳን ሢሠሩ የነበሩ መልካም ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
መተጋገዝ በረመዳን ወር ብቻ የሚፈጸም ባለመኾኑ አሏህ ያዘዘውን የመረዳዳት ሥርዓት ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት። አንድነትን እና መከባበርን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሊያስቀጥል እንደሚገባ አንስተው ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ ሰላምን ለማጽናት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
“እናንተ በምድር ላይ ተዛዘኑ እኔ በሰማይ አዝንላችኋለው ይላል አሏህ” ያሉት ሼህ ኢብራሂም መጨካከን ዋጋ እያስከፈለን ስለሚገኝ ለሰው ማዘንን እና ለሰላም መትጋትን ልናስቀድም ይገባል ብለዋል። የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የእስልምና ሃይማኖት መገለጫ ሰላም በመኾኑ የፆሙን ወቅት ለከተማችሁ ብሎም ለሀገራችሁ ሰላም በመጸለይ አሳልፋችኋል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ በታሪኳ አብሮነትን እና አንድነትን አጠናክራ የቀጠለች ስለመኾኗም አስገንዝበዋል። መገዳደል እንዲቆም አብሮነት እና አንድነትን ለማስቀጠል መንግሥት እየሠራ መኾኑን አንስተው የሃይማኖት አባቶች ሰላም እንዲጸና ማስተማር አለባቸው ብለዋል።
ጎንደር አባቶች በአብሮነት የገነቧት ከተማ በመኾኗ የጎንደርን ከፍታ ለማስቀጠል አብሮነትን በማጠናከር መሥራት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። የጎንደርን ከተማ ልማት ለመደገፍ እያደረጋችሁት ያለውን ድጋፍ አጠናክራችሁ ልትቀጥሉ ይገባል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንኳን ለ1ሺህ 446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል አደረሳችሁ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!