
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሩጫው ፈፅሞ መዘናጋትን ከማትሻ ሽርፍራፊ የጊዜ ዑደት ጋር ነው፤ ምክንያቱም በአንዲት ባልታደለች የጊዜ ቁራጭ ውስጥ ሕይወት ሊያልፍ ይችላልና፡፡
ግብግቡ እስትንፋስ እስከመቀጠል የሚደርስ ነው፤ ትግሉ ከማያቋርጠው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ፍትጊያው ሕይወት እንድትቀጥል ብቻ ሳይሆን ትውልድ እንዲቀጥልም አዳዲስ ጨቅላ ሕጻናትን ከማኅፀን ዓለማቸው ወደዚች ዓለም በሰላም ማሸጋገር ነው፡፡ ሙያዊ ግዴታው ምጣኔ ሀብታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቀለምን እና ማንነትን መሠረት ሳያደርግ የጤና ችግረኞችን ሁሉ በእኩል ዐይን መንከባከብ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ግን የማይመች የሥራ አካባቢ፣ አሳዛኝ ክስተት እና ቅስም ሰባሪ ሁነትን እንደሰው ማስተናገድም ግድ ይላል፡፡ እንደኢትዮጵያ ዓይነት የታዳጊ ሀገር ነርስ መሆን ደግሞ ጭንቁ እልፍ፣ መከራው እጥፍ፣ የልብ ስብራቱ ጠሊቅ እና ጎደሎው ብዙ ነውና ችግሩን ለመረዳት የግድ ሐኪም መሆንን አይጠይቅም፡፡
ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነርሶች ቀን ይከበራል፡፡ እኛም በዚህ ዓለማቀፋዊ የጤና ቀውስ ወቅት ራሳቸውን አሳልፈው ለሌላው የሚሰጡ ነርሶቻችንን ልናመሠግናቸው ወደድን፡፡ ኮሮናን ድል ለመንሳት ራሳቸውን ከቤተሰቦቻቸው ነጥለው በለይቶ የሕክምና መስጫ ቦታ (ኳራንታይን) ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡
ሲስተር ንግሥት ዓለማየሁ እና አበበ ይሁን በኮሮና ቫይረስ የሕክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ “የተለያዬ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስሪት ያለውን ማኅበረሰብ ማገልገል ከባድ ቢሆንም ሙያዊ ኃላፊነት ነውና ወቅታዊውን የጤና ስጋት ለመከላከል እና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡
“ነርስ ስትሆን ኃላፊነትህ ዕርዳታህን ለሚፈልጉ ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መስጠት ነው” ያለው አበበ ቅንነትን፣ ታጋሽነትን፣ መረዳትን እና ማገልገልን ሁሉ የተሰጠ ሙያ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “ነርስ ስትሆን የደስታህ ምንጭ ሕሙማንህ ሲያገግሙ ማየት የመሆኑን ያክል የሐዘንህ ምክንያቱም የታማሚዎችህ ሐዘን በመሆኑ የምታስተናግደው ስሜት ቅይጥ ነው” ይላል፡፡
“ነርስ መሆን ያውም እንደ እኔ ሴትነትን ከሙያዊ ኃላፊነት፣ እናትነትን ከትህትና ጋር አስተሳስሮ ማገልገልን የሚጠይቅ ሙያ ነው” ያለችን ደግሞ ሲስተር ንግስት ናት፡፡ ችግሮቹ ብዙ ቢሆኑም ውጤቱ አስደሳች እና የሚለካ በመሆኑ ደስ እንደሚላት ነው የተናገረችዉ፡፡
“ማኅበረሰባችን የራሱ የሆነ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ስሪት አለው” ያሉት ነርሶቹ እንደወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ዓይነት ወረርሽኝ ሲከሰት ፈተናው ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሕይወት ላለ ይቅር እና ላለፈ ወገናችንም ቢሆን ክብር ስላለን መኖር ባይቻል እንኳን በማኅበረሰቡ ወግና ባህል መሠረት ሽኝት የሚደረግበት ጊዜ ላይ ለመድረስ ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡ “እኛ ስለእናንተ ማኅበራዊ ሕይወታችንን ረስተንና ቤተሰቦቻችንን ተለይተን በዚህ እንቆያለን፤ እናንተ ደግሞ ስለእኛ በቤታችሁ ቆዩ” ብለዋል ነርሶቹ፤ ሙያው የተናጠል ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጋር የሚሠራ በመሆኑ ለሁሉም የጤና ባለሙያዎች “እንኳን ለነርሶች ቀን አደረሳችሁ” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የነርሶችን ቀን በሚመለከት መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴም “ቀኑን የምናስበው እናንተ ስለሁላችንም ስትሉ ለምትከፍሉት መሥዋዕትነትና ለማመን ለሚከብደው ቁርጠኝነታችሁ ከፍተኛ ዕውቅና በመስጠት ነው” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዮቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡