
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዒድ አል ፈጥር በዓል በባሕር ዳር ከተማ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።
የዛሬ ዓመት በዓሉን ስናከብር በሰላም እጦት እና በአሳዛኝ ድርጊት ነበር ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ያ ሁሉ እንደሚያልፍ፣ ሰላማችን እንደሚመለስ፣ የሕዝባችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ መልስ መስጠት እንደምንችል ቃል ገብተን ነበር ነው ያሉት።
“የዛሬ ዓመት የመስገጃ ቦታ እንደምንሰጥ ቃል በገባነው መሠረት ቃላችን ጠብቀን አስረክበናልም” ብለዋል።
በዓመቱም የክልሉ እና የአካባቢው ሰላም እየተመለሰ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ በዚህም ስኬት እየተገኘበት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማዋን ልማት ከወትሮው በተሻለ ደረጃ ማሳደግ የተቻለበት መኾኑንም ተናግረዋል።
ከተማዋ እያማረባት እና እየፈካች መኾኗንም አብራርተዋል። መሪዎች እና የከተማዋ ሕዝብ በአንድነት በመሥራታቸው የታሰበውን ማሳካት እንደተቻለም አስገንዝበዋል።
“በዚህ ቦታ ደስ ብሏችሁ በማየቴ እና የደስታችሁ ተካፋይ በመኾኔ ደስተኛ ነኝ” ነው ያሉት።
“በደስታም በሀዘንም አንድ ነን፣ አንለያይም” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሚጠይቀውን ጥያቄ ሕግ እና ሥርዓትን ተከትለን ከመመለስ ወደ ኋላ አንልም ብለዋል።
አንድ ኾነን ሰላማችን እናስከብራለን፤ የከተማችንን ልማትም ወደፊት እናራምዳለን፤ የከተማችን ሰላም እና ልማት ሲረጋገጥ የምትመች ከተማ ትኾናለች ሲሉ ነው ያብራሩት።
ከተማዋን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ የማድረግ ጉዞ በአንድነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለሰላም እና ለልማት ሲያደርገው የነበረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በባሕር ዳር ከተማ እየተሠራ ያለው ልማት ከተማዋን ተመራጭ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዓሉ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ ያለው ለሌለው የመስጠት እንዲኾንም ተመኝተዋል።
ተዛዝኖ እና ተረዳድቶ የመኖር ባሕል የዘወትር ተግባር ሊኾን እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!