
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ እስልምና ምክር ቤት ለ1ሺህ 446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ እስልምና ምክር ቤት ዋና ሠብሣቢ ሼህ አሕመድ አወል የረመዳን የመጨረሻዋ ቀን ሕዝበ ሙስሊሙ ከአሏህ የሚሸለምበት ቀን መኾኑን ገልጸዋል። ረመዷን የፍቅር፣ የሰላም እና የመጠያየቅ ወር መኾኑንም ነው የገለጹት።
ዋና ሠብሣቢው እንዳሉት በረመዳን ወር በተለይም ደግሞ በ27ኛው ሌሊት “ለይለቱል ቀድር” ትባላለች። በዚች ቀን ሕዝበ ሙስሊሙ ለረጅም ሠዓታት ሶላት በመስገድ፣ በጸሎት፣ ዝክር በማድረግ እና እንዲሁም የአሏህን ይቅርታ እና ምኅረት አብዝቶ በመለመን ሌሊቱን ያሳልፋል። ቀኗ ከ83 ዓመት በላይ በረከት ያላት የተቀደሰች ሌሊት በመኾኗ የሰላም ሌሊት ትባላለች ነው ያሉት።
ረመጇን አማኙ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ በተለያየ ጊዜ ያጠፋውን ይቅርታ የሚለምንበት በመኾኑ የይቅርታ ጊዜ ተደርጎ ይወሰዳል። በእስልምና ሃይማኖት ከሦስት ቀን በላይ ቂም ይዞ መቆየት ባይፈቀድም በረመዷን የቆየ ቂም በይቅርታ ተሽሮ፣ እርቅ ወርዶ አብሮነት የሚጠናከርበት ወር ነው ብለዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ስለ ሰላም፣ ይቅርታ እና ፍቅር በመስበክ ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን እንዲተገብር አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶች የሀገር ምሰሶዎች በመኾናቸው ማኅበረሰቡን በሃይማኖታዊ ግብረ ገብ የማነጽ አባታዊ ግዴታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም በተለይም ደግሞ ወጣቶች ቂምን በመሻር ሰላምን አጥብቀው እንዲይዙ እና ዘመን ያመጣውን ቴክኖሎጅ ለመልካም ነገር እንዲጠቀሙበትም መክረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!