
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) የቻይና የሐኪሞች ቡድን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝምባብዌ ገባ፡፡
ከማዕከላዊ ቻይና ሁናን ግዛት መነሻቸውን ያደረጉት ሐኪሞቹ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ የሕክምና ቁሳቁስ መውሰዳቸውም ታውቋል፡፡ አጋዥ የመተንፈሻ መሣሪያዎች (ቬንትሌተሮች)፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ የመመርመሪያ መሣሪያዎችና ሌሎች የሕክምና ቁሳቁስ ነው የሐኪሞች ቡድን ለሀገሪቱ ያስረከበው፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከሉ ሥራ ልምድ ያላቸው በመሆናቸውም ለዝምባብዌ ሐኪሞች ሥልጠና እንደሚሰጡ ነው የተገለጸው፡፡ ቫይረሱን እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ ሰዎችን መመርመርና የሕክምና ዕርዳታ መስጠት ስለሚቻልባቸው መንገዶችም እንደሚያሰለጥኑ ታውቋል፡፡
በዋና ከተማዋ ሀራሬ በሚገኘው ሮበርት ሙጋቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለቡድኑ በተደረገው አቀባበል የተገኙት በዝምባብዌ የቻይና አምባሳደር ጉ ሻዎ ቹን የሁናን ግዛት መንግሥትና የሕክምና ተቋማቱ ላደረጉት በጎ ተግባር አመሥግነዋል፡፡ የሐኪሞችን ልዑክም ረዥም ርቀትን አቆራርጠው በበጎ ተግባሩ ለመሳተፍ በመምጣታቸው አመሥግነዋቸዋል፡፡ “በጋራ በምናደርገው መተጋገዝ የኮሮናቫይረስን እናሸንፋለን” ብለዋል አምባሳደር ጉ ሻዎ ቹን፡፡
ሀገራቱ ዘመናትን ተሻገረ የመተጋገዝ ታሪክ እንዳላቸው በማስታዎስም የጋራ ጠላት የሆነውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመተባበር ማሸነፍ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡
የቻይናዋ ሁናን ግዛት ከ1985 (እ.አ.አ) ጀምሮ እስካሁን 17 የሐኪሞች ቡድንን ወደ ዝምባብዌ በመላክ ድጋፍ ማድረጓን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
የቻይና ሐኪሞች ቡድን የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በአስማማው በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዮቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡