
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢድ ወር ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ልዩ ወር ነው። ይህ ልዩ ወር በዕምነቱ ተከታዮች ከመወደዱም በላይ ቅዱስ ወር እያሉም ይጠሩታል። ይህ ወር ማሳረጊያው ታዲያ ኢድ ይኾናል። ይህ ቀን የሃይማኖቱ ተከታዮች በልዩ ዝግጅት እና በተለያዩ የሃይማኖቱ አስተምሮ ተግባራት ነው የሚከበረው።
በዚህ ቀን ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከሚሳተፉባቸው ሃይማኖታዊ ተግባራት መካከልም የኢድ ሶላት ይገኝበታል። ዛሬም ስለዚሁ ሥነ ሥርዓት እንቃኛለን።
ስንት አይነት የኢድ ሶላት አሉ? በደሴ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት ኡስታዝ ሼህ ሀሰን ሀሚድ ስለሶላት ሲገልጹ የበዓል ሶላት ሁለት አይነት እንደኾኑ ነግረውናል። ይህም የኢድ አል ፈጥር ሶላት እና የኢድ አል አድሃ ሶላት እንደሚባሉም ነው የጠቆሙት።
በእስልምና ይህ ወር ቅዱስ ወር እንደሚባል እና ቁርዓን የወረደበት ወር በመኾኑ የዕምነቱ ተከታይ የኾነ ሁሉ በዚህ ወር በትጋት በመጾም እና በመልካም ሥራ ሁሉ እንደሚተጋ አስገንዝበዋል። በዚህ ወር የሚከናወነው ጾም እና መልካም ሥራ የሚጠናቀቀው በኢድ ሶላት ነው የሚሉት ሼሁ በዚህ ሥነ ሥርዓት ሁሉም አማኝ ይሳተፋል ነው ያሉት።
የኢድ ሶላት የሚሰገድበት ምክንያት? ሼህ ሀሰን ሀሚድ ሶላት የሚሰገደው የተቀደሰውን ወር ሙሉ በሰላም እና በመልካም ተግባር ላዘለቀው አላህ ምሥጋና ለማቅረብ እና አላህን ለመቀደስ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የኢድ ሶላት መቼ እና እንዴት ይሰገዳል? በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በፍቅር እና በደስታ የሚተገበረው የኢድ ሶላት የሚሰገደው ረፋድ ሰዓት እንደኾነ የነገሩን ሼህ ሀሰን ሀሚድ የሚሰገደው ከመስጂድ ውጭ በተዘጋጀ ሰፊ ሜዳ ላይ እንደኾነም ነው ያብራሩት።
የኢድ ሶላት ምንን ይገልጣል? ሼህ ሀሰን ሀሚድ እንደነገሩን ይህ ሶላት የዓለምን ፍጻሜ የሚያሳይ እንደኾነ ገልጸው ሰዎች ከተፈጠሩ ጀምሮ እስከዓለም ፍጻሜ ያለውን ሁኔታ የሚያስታውሱበት ጊዜም እንደኾነ ተናግረዋል።
የአንድ አካባቢ ሰዎች በቀን መስጅድ ውስጥ አምስት ጊዜ፣ በየሳምንቱ ደግሞ አርብ ሲሠባሠቡ ሰፋ ያለ ስብስብ ይታያል። በየዓመቱ በሁለቱ የበዓል ሶላቶች ደግሞ ሲሠባሠቡ በጣም ሰፊ ሕዝብ ኾነው ይሠባሠባሉ።
ይህም አላህ በመጨረሻው ቀን እንዲሁ የሰው ልጆችን ሠብሥቦ ፍርድ የሚሰጥበትን ቀን አስታውሰው ሰዎች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እና ለመልካም ተግባር እንዲተጉ የሚያሳስብ የሶላት ሥነ ሥርዓት ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
የኢድ ሶላት ለምን ከመስጅድ ውጭ ኾነ? ሼህ ሀሰን ሀሚድ እንደነገሩን በዚህ ሶላት ጊዜ ሰዎች በአንድ ላይ ስለሚሠባሠቡ ደክሞ የታየውን እና ያጣ የነጣውን አይዞህ ብሎ ባለው ሁሉ ለማገዝ፣ የጠፋውን ለመፈለግ እና ለመደገፍ ታሳቢ ተደርጎ እንደተደረገም አስገንዝበዋል።
በዚህ ሶላት እነማን ይሳተፋሉ? ሼህ ሀሰን እንደነገሩን በመስጂድ ሁልጊዜ በሚካሄደው ሶላት ሴቶች እና ሕጻናት መገኘት እንደማይገደዱ ገልጸው በኢድ ሶላት ጊዜ ግን ከልጅ እስከ አዋቂ እንደሚሳተፍ ነግረውናል። በዚህ ሶላት ላይ ከወር አበባ ያልነጹ እንኳን ቢኾኑ በቦታው ተገኝተው አስፈላጊውን ሥነ ሥርዓት በሚዘጋጅላቸው ቦታ ኾነው እንዲካፈሉ የግድ እንደሚኾን ነው ያብራሩት። ስግደት ግን እንደማይሰግዱ ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!