
ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንኳን ለ1446ኛው ዓመተ ሂጂሪያ የኢድ አል ፊጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት። የዒድ-አልፊጥር በዓል በሂጅራ አቆጣጠር የተከበረውን የረመዳን ወር ተከትሎ የሸዋል ጨረቃ ሰትወጣ በታላቅ እሰላማዊ ሥርዓት የሚከበር በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች በደስታ፣ በመተሳሰብ እና በአብሮነት ሰሜት የሚያሳልፉት ልዩ ውበትና ድምቀት ያለው በዓል ነው ብለዋል።
“ዒድ አል ፈጥር የምስጋና፣ የበጎ አድራጎት እና የወንድማማችነት እኅትማማችነት” በዓል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
“በረመዳን ወቅት ውስጥን ለመመልከት የሚጠቅም ነው። ውስጣቸውን የተመለከቱ ሰዎች ምስጋና ገንዘባቸው ነው፡፡ ጾሙ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ራስን ገዝቶ ለመሰባሰብ ይጠቅማል” ነው ያሉት፡፡
“የዒድ ሌላው ዕሴት በጎ አድራጎት ነው። ዐቅም ለሌላቸው፣ ሁኔታው ላልተሟላላቸው ወገኖች መልካምን ነገር ማድረግ፡፡ ዝምድናን፣ ዘርን ወይም እምነትን ሳይመለከቱ ሰውን በሰውነቱ ብቻ መርዳት ነው፡፡ የጾም ምንዳዕ ሙሉ የሚሆነው በጎ አድራጎት ከተጨመረበት ነው፡፡ ትልቅነትን ከውስጣችን፣ ታላቅነትንም በመካከላችን ፈልገን የምናገኝበት ነው” ብለዋል።
ሮመዳን የራህመትና የእዝነት ወር በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ በሮመዳን ወር ያሳያቸውን አንድነትና መተዛዘን እንዲሁም መደጋገፍና ለሰላም ሲያደርጋቸው የነበሩ ጸሎቶችን በሌሎች ጊዚያትም አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!