የነገዋ የሴቶች ተሐድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጣኞችን አስመረቀ።

60

አዲስ አበባ: መጋቢት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የነገዋ የሴቶች ተሐድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በ17 ዓይነት የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 380 ሠልጣኞች አስመርቋል።

የነገዋ የሴቶች ተሐድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለሥነ ልቦና ተፅዕኖ የተጋለጡ ሴቶችን በተለያየ ክህሎት እና ሙያ በማሰልጠን ያስመርቃል። የስልጠናው ዓላማ ሰልጣኞች የትላንት ሕይታቸውን እንዳይደግሙ እና የነገዋን ማንነት እንዲሹ በማብቃት ላይ ያተኩራል ተብሏል።

ይህ ማዕከል በሁለተኛ ዙር የሥልጠና መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን ሠልጣኞች አስመርቋል። በምረቃ መርሐ ግብሩም የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማዕከሉ ሲቋቋም ዋና ዓላማው በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ተጋላጭ የኾኑ ሴቶችን መልሶ ማቋቋም ነው ብለዋል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮች፣ መድልኦ እና መገለል በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ የጎላ ነው ብለዋል ከንቲባዋ። ይሄን ማዕከል በቀጣይ ከዚህ በበለጠ በማጠናከር የብዙ ሴቶችን ሕይዎት ለመቀየር በትጋት ይሠራል ነው ያሉት።

ሴቶች ለአደጋ ተጋላጭ እንዳይኾኑ እና ካሉበት የሥነ ልቦና ጫና እንዲወጡ ሁሉም በመተባበር ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።

400 ሠልጣኞች ወደ ግቢው መግባታቸውን የጠቀሱት የማዕከሉ ዋና ዳሬክተር ዶክተር ሂርጳስ ጫላ ከገቡት ሠልጣኞች 380ዎቹ የማዕከሉን መመዘኛ በማለፋቸው እንደተመረቁ ጠቅሰዋል።

ዳሬክተሩ አክለውም የተመረቁ ሠልጣኞች የሥራ እድል እንዲያገኙ ከመንግሥት እና ከግል ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ላይ ነን ብለዋል።

ዘጋቢ:- ራሔል ደምው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአድማ መከላከል አባላት በደብረ ታቦር ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው።
Next article“ትምህርትን ማቃናት ሀገርን ማጽናት ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)