
ጎንደር፡ መጋቢት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከጎንደር ቀጣና የዞን እና የወረዳ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የሴቶች ጥቃት እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ያለመ ውይይት በጎንደር ከተማ አካሂዷል።
በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በክልሉ ረዘም ያለ ጦርነት መከሰቱ፤ ፆታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንደ አዲስ እያቆጠቆጡ መምጣታቸው በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን አስረድተዋል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና በአማራ ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር በርካታ ሴቶች ላይ ጥቃቶች መድረሳቸውንም አረጋግጠዋል።
ጦርነት፣ ድርቅ እና መፈናቀል ፆታዊ ጥቃት እንዲባባስ ያደርጋል ያሉት ኀላፊዋ በጉዳቱ ልክ መረጃ አለመድረስም ጥቃቶችን ለመከላከል እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ነው የተናገሩት።
ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይ የሚደርስ ጥቃት በመኾኑ የሚስተዋለውን ጥቃት በጋራ መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በክልሉ የሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ በመኾኑም የድርሻቸውን እንዲወጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መሰጠታቸውን አስታውሰዋል።
የሃይማኖት አባቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ተሰሚ በመኾናቸው አባቶች በክልሉ የሚስተዋለውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አማኙን በማስተማር መከላከል እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተጋላጮች ላይ ብቻ ሳይኾን በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመኾኑ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በጋራ መከላከል ይገባል ብለዋል።
ፆታዊ ጥቃቶች ለተላላፊ በሽታዎች፣ ለአካላዊ እና ማኅበራዊ ጉዳቶች እየዳረጉ ነው ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቀኑ ቢያድጎ እና የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ባንቺዓምላክ መልካሙ ችግሩን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት እና ለኢኮኖሚ ጥገኝነት ይዳርጋል የሚሉት ኀላፊዎቹ አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮሩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በመድረኩ አሚኮ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት እየሠሩ መኾናቸውን ጠቁመው ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!