
ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በብርሸለቆ መሠረታዊ የውትድርና ማሠልጠኛ ያሠለጠናቸው የ33ኛ ዙር የአድማ መከላከል አባላት በደብረ ታቦር ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በአቀባበል መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ወታደርነት ለዓላማ በመፅናት ሕይወት ከፍሎ ሀገር ለማስቀጠል እና ለሕግ የበላይነት መከበር ዘብ የሚቆም ኀይል ነው ብለዋል።
እናንተ ለሕዝብ እና ለሀገር ለመኖር፣ ለመጠበቅና ለማገልገል ቀድማችሁ የተሰለፋችሁ ናችሁ ብለዋቸዋል።
በዞኑ ተመድበው የመጡ ተመራቂ የአድማ መከላከል አባላት ዘላቂ ሰላም በማስፈን ሕዝባችን ከገጠመው ውስብስብ ችግር እንዲወጣ ኀላፊነት ተጥሎባችኋል ነው ያሉት።
የአካባቢው ሕዝብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በተሟላ መንገድ እንዲያገኝ በቁርጠኝነት ተልኳቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች በመኾን መንግሥት እያደረገ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ በማገዝ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የሠላም እጦት በገጠመበት እና የታጠቁ ኀይሎችን ዓላማ እያከሸፍን በምንገኝበት ወቅት የመጣቹህ በመኾናችሁ ልዩ ያደርጋችኋል ብለዋቸዋል።
የፖሊስ ሙያ በተገቢው መንገድ ከሠራችሁበት የማትደርሱበት የሥልጣን ደረጃ እና እድገት አይኖርም ያሉት ከንቲባው ከመስመር ሊያወጣን የሚሞክርን ኀይል በፅናት በመታገል መዝለቅ ይኖርባችኋል ነው ያሉት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት በዛ ሰላም ከሌለ ልማት የለም፣ ሰላም ከሌለ የዲሞክራሲ ሥርዓት አይታሰብም ብለዋል። ሁሉም ለሰላም መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መኾን እንደሚገባውም አንስተዋል። ለዚህም አብረን እንሠራለን ነው ያሉት።
በማሰልጠኛ ተቋሙ ያገኙትን ወታደራዊ አቅም በመጠቀም ስምሪት ላይ ካሉ ሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት የተሰጣቸውን ተልዕኮ እና ግዳጅ በአግባቡ እንደሚወጡም የአደማ መከላከል አባላቱ ተናግረዋል።
ከደቡብ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በመርሐ ግብሩ የ9ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ኀላፊ ኮ/ር ፀሐይነው ብርሃኔን ጨምሮ ሌሎች የዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን