ማኅበራዊ የትስስር ገጽን ለበጎ ዓላማ እየተጠቀመ ያለው ወጣት፡፡

532

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) ማኅበራዊ የትስስር ገጽን አንዳንዶች ለጥፋት አንዳንዶች ደግሞ ለመልካም ሥራ ሲጠቀሙበት ያታያሉ፡፡ በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የገጹ ተጠቃሚዎች በብዛት ለሰዎች ስለወረርሽኙ የሚያውቁትን መልእክት በማስተላለፍ እና ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ከዚህ በተቀራኒ ደግሞ ስለወረርሽኙ ተገቢ ያልሆኑ መረጃዎችን በማስተላለፍ ኅብረተሰቡ እንዲዘናጋና ወረርሽኙ እንዲስፋፋ የሚያደርጉም እንዳሉ ይነገራል፡፡ ዛሬ ፌስቡክን በመጠቀም ለወገን ደራሽነቱን በተግባር ያሳዬ አንድ ወጣት እናስተዋውቃችሁ፡፡

አቶ ተስፋሁን ደስታ ይባላል፤ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ቲሊሊ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ ወጣቱ ማኅበራዊ የትስስር ገጽን በተለይ ፌስቡክን በመጠቀም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር የተቸገሩ የቲሊሊ ከተማ ነዋሪዎችን እንዲያግዙ ጥረት እያደረገና በሚያገኘው ድጋፍም ሌሎችን እያገዘ ይገኛል። በፌስቡክ ገጹም ሰፊ ቅስቀሳ አድርጎ ለተቸገሩ ሰዎች የባንክ የሒሳብ ደብተር በመክፈት ገንዘብ ማጠራቀም ችሏል፡፡

በአቶ ተስፋሁን ደስታ እገዛ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል ሕጻን እሱባለው አዳነ አንዱ ነው፡፡ ሕጻን እሱባለው በሕጻንነቱ ጀምሮ በእናቱ ወይም በአባቱ እቅፍ የማደግ ዕድሉን አላገኘም፡፡ ይልቁንም በሕጻንነቱ ከተወለደበት አካባቢ ተነስቶ ወደባሕር ዳር በመሄድ የጎዳና ኑሮን እንደተጋፈጠ ነግሮናል፡፡ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ደግሞ ለእርሱና መሰሎቹ የጎዳና ኑሮንም ነፍጓቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ታዳጊው እሱባለው ወደ ትውልድ ቦታው ጓጉሳ ሽኩዳድ ቲሊሊ ከተማ መሄዱን ተናግሯል፡፡

ቲሊሊ እንደገባም የሚበላውና የሚጠጣው እንዳልተቸገረ፣ ከኅብረተሰቡ ድጋፍ እንዳገኘ ተናግሯል፡፡ ሕይወቱን በዘላቂነት ለመምራት እንዲችልም ቅን አሳቢው አቶ ተስፋሁን ደስታ በማኅበራዊ ሚዲያ ከሰዎች ጋር በመነጋገር ገንዘብ አሰባስቦ የሊስትሮ ዕቃ በመግዛት ሥራ እንዲጀምር አድርጎታል፡፡ አሁን ላይ ታዳጊው እሱባለውም “በሥራው ደስተኛ ነኝ፤ ለትልቅ ቁምነገር ለመብቃት ጠንክሬ እሠራለሁ” ብሏል፡፡ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ከፍቶ በሁለት ሳምንት እስከ 220 ብር መቆጠብ እንደጀመረም ተናግሯል፡፡

ወይዘሮ እመቤት ተሰማ ደግሞ ሌለኛዋ በአቶ ተስፋሁን ደስታ ማኅበራዊ የትስስር ገጽ በተሰበሰበ ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑ የቲሊሊ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮ እመቤት በመልሶ ማልማት ከድሮ ቤታቸው ሲነሱ ትክ ቦታ ብቻ እንደተሰጣቸውና የገንዘብ ካሳ እንዳልተከፈላቸው ይናገራሉ፡፡ ትክ የተሰጣውንም 200 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ገንዘብ ባለማገኘታቸው ለሰባት ዓመታት ሳይሠሩት ቆይተዋል፡፡ ጧሪ የሌላቸው አዛውንት ለሰባት ዓመታት ፈታኝ ኑሮ ማሳለፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡

ከዚህ በፊት ወረዳ አስተዳደሩ ዝቅተኛ ነዋሪ መሆናቸውን በማረጋገጥ በወር 300 ብር ድጋፍ እያደረገላቸው ከዚህ ውስጥም 220 ብር ለቤት ኪራይ እየከፈሉ እንደነበር ነግረውናል። አሁን ግን አቶ ተስፋሁን ደስታ ከ35 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ አሰባስቦ 33 ዚንጎ ቆርቆሮ ቤት፣ መጸዳጃ ቤት፣ የቧንቧ ውኃና ሌሎችም ለመኖር የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን የተሟላ ቤት እንዳሠራላቸው ገልጸዋል፡፡ “ተስፋሁንን ከእጄ እና እግሬ አስበልጨ እወደዋለሁ፤ ጤና እና ዕድሜ ይስጠው” ሲሉም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ሌሎች ወጣቶችም መልካም ሥራ ከተስፋሁን መማር አለባቸው ብለዋል፡፡

ቤት ለፈረሰባቸው እናት 15 ሺህ ብር በመሰብሰብ ቤታቸው እንዲጠገን፣ ፍራሽና ብርድ ልብስ፣ 150 ኪሎ ግራም በቆሎ ድጋፍ አድርጎላቸዋል። በከተማዋ በተለያየ ምክንያት ተጥለው የሚገኙ ሕጻናትን አንስተው ለሚያሳድጉ እናት ደግሞ 10 ሺህ ብር አሰባስቦ ለግሷል፡፡ ይህንን መልካም ሥራ እያከናወነ የሚገኘው ወጣት ተሰፋሁን ደስታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የማኅበራዊ ገጽ ትስስርን ለመልካም ሥራ እንዲጠቀሙበት መክሯል፤ ሌሎች ወጣቶችም አቅም ለሌላቸው ሰዎች እገዛ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፏል። በቀጣይም በቲሊሊ ከተማ ከሚገኙ ከምግባረ ሰናይ የወጣቶች ማኅበር ጋር በመቀናጀት ለተቸገሩ ዜጎች እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተናግሯል።

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous articleየዓለም ነርሶች ወገናቸውን ከኮሮናቫይረስ ለማትረፍ እየታገሉ ቀናቸውን እያከበሩት ነው፡፡
Next articleየቻይና የሐኪሞች ቡድን ዝምባብዌ ገባ፡፡