
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ትምህርት ሚኒስቴር በብርቱካን ተመስገን ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሙሉ ማብራሪያ:-
ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ስለሆነችው ብርቱካን ተመስገን ከበደ ከትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠ ማብራሪያ
ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ስለሆነችው ብርቱካን ተመስገን ከበደ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት ስላለው ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በስም ተጠቃሽ በ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረች ቢሆንም የብሔራዊ ፈተናው በወቅቱ በተፈጠረው ዓለም ዓቀፍ የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 02/2013 ዓ.ም እንዲሰጥ መደረጉ ይታወሳል። ተማሪዋም በዚሁ ጊዜ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ መሰናዶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፈተና ወስዳ 392 ውጤት በማምጣት በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምደባ ተደርጎላታል፡፡
ሆኖም ግን ወደተመደበችበት ዩኒቨርሲቲ ያልሄደችና ያልተመዘገበች ሲሆን ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት በተከታታይ የትምህርት ኘሮግራም (ኤክስቴንሽን) ተመዝግባ “በአካውንቲንግና ፋይናንስ” የትምህርት ክፍል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ኘሮግራም ከግቢ ውጭ ሆና ትምህርቷን ስትከታተል የነበረችና ትምህርቷንም ሳትጨርስ ያቋረጠች መሆኑን ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተገኘ መረጃ ያረጋግጣል፡፡
በተቃራኒው በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስርጭት በተላለፈው ፕሮግራም ግለሰቧ በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ተመድባ ወደ ሀሮማያ በመጓዝ ላይ ሳለች አውቶቡስ ውስጥ ባገኘቻት ደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ተመድባ በመጓዝ ላይ ካለች ሌላ ተማሪ ጋር በመነጋገር ሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የነበራትን ጉዞ በመሰረዝ ወደ ደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ሄዳ ለመማር ተመዝግቢያለሁ ማለቷ ከእውነታውና ከአሰራር ውጭ የሆነና በፍጹም ወደ ደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ያልሄደችና ምዝገባም ያላደረገች መሆኑ የዩኒቨርስቲው መረጃ ያስረዳል።
በዚህ አጋጣሚ ማንኛውም አይነት የአዲስ ተማሪዎች ምደባ የሚከናወነው በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ እንጂ በዩኒቨርስቲዎች ደረጃ የማይፈቀድ መሆኑም ለማሳዎቅ እንወዳለን።
በመሆኑም፤
1. በማኅበራዊ ሚዲያው እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ጋር ካለው እውነታ ውጪ የሆነ መሆኑን እንገልጻለን፤ ይህንኑ የሚያረጋግጡ መረጃዎችም ከዚህ ማብራሪያ ጋር ተያይዘዋል፤
2. ይህንን የተሳሳተ መረጃ መሠረት በማድረግ በውስን ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስተጓጎል የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች የሚከናወኑባቸው፣ ዕውቀትና እውነት የሚሰርጽባቸው በእውነትና በዕውቀት የሚመሩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል።
3. የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (EBS) ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው እንደማንኛውም ሚዲያ ጉዳዩን ከማሰራጨቱ በፊት ከዩኒቨሲቲዎቹ ወይንም ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘውን መረጃ ማጣራት ሲገባው ይህንን ጉዳይ ሳያጣራ በቀጥታ አየር ላይ ማዋሉ ሕዝቡን ከማሳሳት ባሻገር የዩኒቨርስቲዎቹን ገጽታ በማበላሸትና በማጠልሽት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ ኀላፊነቱን ሊወስድ ይገባል።
ስለሆነም እንደዚህ አይነት የፈጠራና የሀሰት ቅንብሮችን መሠረት አድርጎ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚደረግ የመማር ማስተማር እንዲሁም የምርምር ሥራዎቻቸውን ሊያውኩ የሚችሉ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴና ተግባር ፍፁም ተቀባይነት የሌላቸውና ይህንንም ሆን ብለው በሚፈጽሙና በሚገፉ አካላት ላይ ከፍተኛ አሥተዳደራዊ እርምጃ አለፍ ሲልም በተቋማቱ ንብረትም ሆነ በሰው ላይ ለሚደርስ አደጋና ጉዳት ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማሳሰብ ይወዳል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ የዩኒቨርሲቲዎች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሁም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙበት መሠረታዊ ተልዕኮዎች በመረዳት የተቋማቱን ደህንነትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ተገቢውን ጥበቃ እንድታደርጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር
መጋቢት 19 /2017 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
