የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የጤናማ ቤተሰብ መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑን የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ።

24

ደባርቅ: መጋቢት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጤና ተቋማት የሚሰጡ የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ለእናቶች እና ልጆች ጤንነት ጠቀሜታቸው ከፍተኛ መኾኑን የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። የደባርቅ ጤና ጣቢያ የዕናቶች አገልግሎት ባለሙያዋ ሲስተር ሔለን ጥላሁን ባለፉት ጊዜያት እናቶች ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና ያላቸው ግንዛቤ እና ትኩረት አናሳ እንደነበር ገልጸዋል።

የሥነ ተዋልዶ ጤና ከሥነ ተዋልዶ ሥርዓት፣ ከተግባሮቹ እና ከሂደቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የበሽታ ወይም የአካል ጉዳት አለመኖር ብቻ ሳይኾን የተሟላ የአካል፣ የአዕምሮ እና የማኅበራዊ ደኅንነት ሁኔታ መጠበቅ እንደኾነም ተናግረዋል። በተለያየ ጊዜ በተሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የትውውቅ ሥራዎች ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

በጤና ተቋማት ከሚሰጡ አገልግሎቶች በተጨማሪም በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚሰጡ የቤት ለቤት አገልግሎቶች ጠቀሜታ እንዳላቸውም አንስተዋል። በእርግዝና ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ሥነ ልቦናዊ ጫናዎችን በመረዳት ከሕክምና ድጋፉ ጎን ለጎን ባለሙያዎች ከተገልጋዮች ጋር በመቀራረብ ምክክር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የደባርቅ ጤና ጣቢያ የእናቶች እና ሕጻናት ኬዝ ቲም አሥተባባሪ እንየው አደራጀው የስነ ተዋልዶ ጤና የወንዶችንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እና ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤናማ ቤተሰብ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል። የእርግዝና ክትትል እና ድጋፍ ከሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች መካከል አንዱ ነው። የደም መፍሰስ፣ ከምጥ ቀድሞ የእንሽርት ውኃ መፍሰስ፣ ከፍተኛ የራስ ምታት እና ሌሎችም በእርግዝና ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ እክሎችን ቀድሞ ለማወቅ እና መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል በመኾኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም መክረዋል።

በደባርቅ ጤና ጣቢያ ተገኝተን ያነጋገርናቸው እናቶች እንደገለጹት በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል እና ቀጣይነት ላለው የእናቶች እና ልጆች ጤንነት ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የደባርቅ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ደጀን ከሕክምና ክትትል እና ድጋፉ በተጨማሪ ከባለሙያዎች የሚያገኙት ምክር ሥነ ልቦናዊ መነቃቃትን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ እድላዊት ጥገት የእርግዝና ክትትል ማድረግ ለእናቶች ደኅንነት እና ለልጆች ጤንነት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article1446ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ማጠናቀቁን የደሴ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleትምህርት ሚኒስቴር በብርቱካን ተመስገን ጉዳይ ማብራሪያ ሰጠ።