ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

18

ጎንደር: መጋቢት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017/18 የምርት ዘመን የአማራ ክልልን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የዕቅድ ትውውቅ እና የቅድመ ዝግጅት ሥራን በተመለከተ በጎንደር ከተማ ውይይት ተደርጓል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን በዋና ዋና ሰብሎች ላይ ትኩረት በማድረግ የምርት ጭማሪ ለማስመዝገብ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር እና መሰል የቅባት አዝዕርት ምርቶች ላይ መሥራት የትኩረት አቅጣጫ መኾኑም ተናግረዋል። በክልል ደረጃ ያለውን የምርት መጠን ለመጨመር በሚደረገው ጥረት የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሮችን በሚገባ ማገዝ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር በመሸፈን ከ187 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱንም ተናግረዋል። ከሚመረተው ከ187 ሚሊዮን ኩንታል ባለይ ምርት 113 ሚሊዮን ገደማ የሚኾነው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚውል ነው ተብሏል። ቀሪው ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች እና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ይኾናል ነው ያሉት።

ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር በሚደረገው ጥረት የግብዓት አቅርቦት ቀዳሚው ጉዳይ በመኾኑ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል። በምርት ዘመኑ ከ8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዶ እስከ አሁን ድረስ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን ገልጸዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦትም በሚፈለገው ልክ ለማዳረስ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የታቀደውን ምርት ለማሳካት አቅምና ሃብት ያላቸው አካባቢዎችን የሜካናይዜሽን አስተራረስን እንዲተገብሩ የማድረግ ተግባርም ይሠራል ነው ያሉት። በሌላ በኩል በመኸር ሰብል ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸረ አረም እና ጸረ ተባይ በሽታዎችን ለመከላከል የክልሉ መንግሥት ዝግጁ መኾኑንም አንስተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሰብል ልማት ቡድን መሪ ዋለ መርሻ በሰሜን ጎንደር ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን ከ150 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር በመሸፈን ከ3 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ሠርቶ ማሳያ ባለሙያ ቻላቸዉ አቸነፍ በዞኑ በምርት ዘመኑ ከ520 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር በመሸፈን ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

ተኪ ምርቶችን እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ዘጋቢ: ደስታ ካሳ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለፊቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleየጡት ካንሰር መንስኤ እና መፍትሔዎቹ