“ፖሊስ ለሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን ጠብቆ ሢሠራ ታማኝነትን ያገኛል” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ።

44

ሁመራ: መጋቢት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከሁሉም የከተማ አሥተዳደሮች እና ወረዳዎች ለተውጣጡ ምድብተኛ ፖሊሶች ኅብረተሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ምርመራ አቅምን ማጠናከር አላማው ያደረገ ሥልጠና በሁመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሥልጠናው ከዚህ በፊት የፖሊስ እና የጸጥታ መዋቅሩ የሠራው ሥራ የሕዝቡን ፍላጎት ማሟላት እና አለማሟላቱን ለማሳየት ይረዳል ያሉት የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መመሪያ ምክትል ኀላፊ ጌታቸው ሙሉጌታ ናቸው። ሠልጣኞች ሚናቸውን በማወቅ እና በመለየት ተግባሮቻቸውን በትክክል መፈጸም እንደሚገባቸው ያነሱት ምክትል ኀላፊው ዞኑ የብዙዎች አይን ማረፊያ በመኾኑ ብቁ የጸጥታ ኀይል ኾኖ መገኘት ይገባል ብለዋል።

የወንጀል መከላከልን በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ ለማከናወን የሥልጠናው ሚና የጎላ እንደሚኾንም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። “ፖሊስ ለሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን ጠብቆ ሲሠራ የሕዝብ ታማኝነትን ያገኛል” ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው።

እያንዳንዱ የፖሊስ አባል የተቀበለውን የሕዝብ አደራ በማሰብ እና የግል ጥቅም ሳያሸንፈው ማገልገል እንደሚገባውም አንስተዋል። የማንነት ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ይጠናቀቁ ዘንድ ሰላም እና ጸጥታን በማረጋገጡ ረገድ የዞኑ የፖሊስ መዋቅር ከፍተኛ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም ኮሎኔል ደመቀ ጠቅሰዋል።

እርስ በእርሳችን በመማማር እና በመናበብ የሕዝባችን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል ዓቅም መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleክሎኒንግ አለያም ስዋፒንግ ምንድን ነው?
Next articleርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለፊቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።