የዓለም ነርሶች ወገናቸውን ከኮሮናቫይረስ ለማትረፍ እየታገሉ ቀናቸውን እያከበሩት ነው፡፡

171

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) የዓለም የነርሶች ቀን ነርሶች ወገኖቻቸውን ለማትረፍ ከምንጊዜውም በላይ ሕይዎታቸውን ለአደጋ ባጋለጡበት ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡

ዛሬ ግንቦት 4/2012 ዓ.ም የዓለም የነርሶች ቀን ነው፡፡ የዓለም ነርሶች ካውንስል እ.አ.አ ከ19 65 ጀምሮ ነው ቀኑን ማክበር የጀመረው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀኑ እንዲከበር የተወሰነው ግን እ.አ.አ ግንቦት 12/19 74 ላይ ነው፡፡ መነሻ ምክንያቱ ደግሞ የዘመናዊ ነርሲንግ ሙያ መሥራች በመባል የሚታወቁትን የፍሎረንስ ናይትንጌልን የልደት ቀን ለማስታዎስ ነው፡፡

በእርግጥ የነርሲግን ሙያን በማዘመንና በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ በማምጣት የሚመሠገኑት ፍሎረንስ ናይትንጌል የተወለዱት እ.አ.አ ግንቦት 12/18 20 እንደሆነ ነው የሕይዎት ታሪካቸው የሚያስረዳው፡፡ ከባለጸጋ የእንግሊዝ ቤተሰብ የተወለዱት ነርሷ በወቅቱ ለሙያው የነበረው ዝቅተኛና የተዛባ አስተሳሰብ እንዲስተካከል ብዙ ጥረት እንዳደረጉና ለውጥም እንዳስመዘገቡበት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

በህክምና ርዳታ እጦት የሚጠፋውን ሕይዎት በመታደግ በኩልም ስማቸው ይነሳል፡፡ ለህሙማን እንክብካቤ ማድረግ ያለውን ጥቅም በማስረዳት የዘመኑን አመለካከት ስለመቀየራቸውም ነው የሚነገረው፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በየዓመቱ የነርሶች አስተዋጽዖ እየታሰበ እንዲመሰገኑ እየተደረገ ነው፤ ከጤና አጠባበቅ፣ ጤናማ አመጋገብ፣ ጤናማ አካባቢ፣… ጋር የተያያዙ መልዕክቶችም እየተላለፉበት ነው፡፡ በዕለቱ ለነርሶችም ለሙያቸው አጋዥ ቁሳቁስ እንዲቀርቡላቸው ይመከራል፡፡

የዘንድሮው የዓለም የነርሶች ቀን ደግሞ ዓለም በኮሮናቫይረስ እየተፈተነች ባለችበት ጊዜ ነው እየተከበረ ያለው፡፡ እናም ነርሶች፣ ሌሎች የጤና ባለሙዎች እና ከጤና ጋር የተያያዘ ሥራ ላይ የተሠማሩት ከኮሮናቫይረስ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠው የሕሙማንን ሕይዎት ለማትረፍ ሕይዎታቸውን አስይዘው ሙዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም ለዚህ ምሥጋና አቅርቧል፡፡ ሁሉም የነርሶችን ፋይዳ እንዲረዳና እንዲያመሠግናቸውም ጥሪ አቅርቧል፡፡

በአስማማው በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዮቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበኩር የግንቦት 03/2012
Next articleማኅበራዊ የትስስር ገጽን ለበጎ ዓላማ እየተጠቀመ ያለው ወጣት፡፡