‎ሀዋሳ ከተማ የፊቼ ጫምባላላ በዓልን በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።

37

አዲስ አበባ: መጋቢት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‌‎ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል በድምቀት ለማክበር ሀዋሳ ከተማ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶችን እየተቀበለች ትገኛለች።

አሚኮ ሀዋሳ ተገኝቶ የበዓሉን ቅድመ ዝግጅት ተመልክቷል። ፊቼ ጫምባላላ በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ የአዲስ ዘመን መለወጫ እና ማብሰሪያ ኾኖ የሚከበር ታላቅ በዓል ነው። ይህ በዓል በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ የተመዘገበው ፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል ከሀገር ሀብቶችና ቅርሶች መካከልም አንዱ ነው።

በዓሉ ዘንድሮ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ መጋቢት 18 በሲዳማ ባሕል አዳራሽ፣ መጋቢት 19/2017 ዓ.ም በሶሬሳ ጉዱማሌ በተለያዩ ትዕይንቶች ታጅቦ በድምቀት ይከበራል።

ፊቼ ጫምባላላ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የመረዳዳት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት ነው። በዓሉ የሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለወጫ በዓል ብቻም ሳይኾን የቆየ ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ይቅርታ የሚሰፍንበት የእርቅ እና የሰላም በዓልም እንደኾነ ይነገርለታል።

አሚኮም ሀዋሳ ከተማ ተገኝቶ ለተመልካች፣ አድማጭ እና አንባቢያን መረጃዎችን በሁሉም አማራጮች እያደረሰ ይገኛል።

ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ- ከሀዋሳ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ባላችሁ ዕውቀት እና ክህሎት ብቻ ሳይኾን በመሰዋእትነት ጭምር ሀገርን የሚያስከብር የሙያ ባለቤት ናችሁ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleክሎኒንግ አለያም ስዋፒንግ ምንድን ነው?