
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን አህጉር አቀፍ የፓን አፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባዔ እንደምታስተናግድ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) አህጉር አቀፍ ጉባኤውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ጉባኤው “የወጣቶችን አቅም ለበለጸገች አፍሪካ” በሚል መሪ መልዕክት ይካሄዳል ብለዋል። ጉባኤው ከመጋቢት 25/2017 ዓ.ም እስከ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም ለተከታታይ ሦስት ቀናት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል ነው ያሉት።
የጉባኤው ዋና ዓላማ የበለጸገች እና ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን ለመገንባት ወጣቶች የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት የፓን አፍሪካኒዝም ስሜትን ለማስረጽ እና የወጣቶችን የዲፕሎማሲ አቅም ለማሳደግ ታልሞ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ወጣቶች የለውጥ መሪ ኾነው አፍሪካን ወክለው በዓለም መድረክ ለአህጉሪቱ ጥቅም እንዲሠሩ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እና ማብቃት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ53 የአፍሪካ ሀገራት ከ1ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በጉባኤው ወጣት መሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የወጣት ማኅበራት፣ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተው ስለወጣቶች በስፋት ይመክሩበታል ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!