
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማስተርካርድ ድርጅት በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትን ለማስፋፋት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች የቨርቹዋል እና የፊዚካል ማስተርካርድ አገልግሎቶችን በሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያቸው እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ይህ ስምምነት ለፈጣን የንግድ እንቅስቃሴዎች እና ለዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነቶች ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። ደንበኞቻችን በሞባይል ስልካቸው አማካኝነት ዓለም አቀፍ የክፍያ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረጋችን ደስተኞች ነን ነው ያሉት።
የማስተርካርድ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ማስተር ማርክ ኤሊዮት ማስተርካርድ በዓለም ከ200 በላይ ሀገሮች ተጠቃሚዎች እንዳሉት ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። ስምምነቱ በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያዎችን ባሕል ለማስፋፋት ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ የኦንላይን ግብይቶችን እንዲፈጽሙ እና ከዓለም አቀፍ ባንኮች ክፍያዎችን እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል ተብሏል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማስተርካርድ ስምምነት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር ትልቅ ርምጃ እንደኾነ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!