
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚገኘውን የቃብቲያ ሁመራ ብሔራዊ ፓርክን ሕልውና ለመጠበቅ እና በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል የምክክር መድረክ በሁመራ ከተማ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ተሾመ አግማስ ብሔራዊ ፓርኩ በቀጣይ ዘላቂ ሕልውና እንዲኖረው እና የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን ከፌዴራል የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመኾን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ፓርኩን ሕልውና ለመታደግ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ምስጋና አቅርበዋል። በዘላቂነት የፓርኩ ሕልውና እንዲጠበቅ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ የአንድ ተቋም ኀላፊነት ብቻ አለመኾኑን የገለጹት ምክትል ኀላፊው የአካባቢው ማኅበረሰብ የፓርኩን ሕልውና በመጠበቅ፣ በማልማት ተሳታፊ እና ተጠቃሚነቱን በተግባር ማሳዬት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን መኮንን ብሔራዊ ፓርኩ በዘላቂነት እንዲለማ እና እንዲጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በፓርኩ የሚታዩ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለማስቆም በቅንጅት ይሠራል ነው ያሉት።
በምክክር መድረኩ በፓርኩ ውስጥ እየታዩ ያሉ ሕገ ወጥ እርሻ፣ የማዕድን ቁፋሮ፣ የደን ምንጠራ እና ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራትን የሚከላከል ግብረ ኃይል ኮሚቴ ተቋቁሞ በቀጣይ ቀናት ወደ ሥራ እንደሚገባም መግባባት ላይ ተደርሷል።
ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልል የሥራ ኀላፊዎች፣ የፓርኩ ባለሙያዎች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች እንደተገኙ ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!