ሀገር አቀፍ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የግብርናውን ዕድገት የሚያመቻች መኾኑን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ገለጹ።

95

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቂያ መድረክ በባሕር ዳር ተካሂዷል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ፖሊሲው አዳጊ ጉዳዮችን የለየ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን የጨመረ፣ የቀደመው ፖሊሲ ያሳካቸውን ውጤቶች ያገናዘበ መኾኑን ገልጸዋል።

በቀደመው ፖሊሲ ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆዩ ዘርፎችን ትኩረት የሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል። የግሉን ዘርፍ በግብርናው ዘርፍ የሚያሳትፍ እና የግብርናውን ዕድገት የሚያሳልጥ መኾኑንም አመላክተዋል። ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሠራም ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የወጡ ፖሊሲዎች እየተተገበሩ ውጤት እያመጡ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ለአርብቶ አደሮችም ትኩረት የሰጠ ፖሊሲ ነው ብለዋል።

ፖሊሲው ከመጽደቁ አስቀድሞ አርሶ አደሮች፣ የምርምር ተቋማት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያሳተፈ መኾኑንም ተናግረዋል። ፖሊሲው ተዛማጅ ዘርፎችን እና ፖሊሲዎችን መመልከቱንም ገልጸዋል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በተገቢው ማየቱንም ተናግረዋል። የማኅበራዊ፣ የሰው ሃብት ልማትን እና ዘመናዊ ግብርናን የመፍጠር ተግባርን የፈተሸ መኾኑንም ገልጸዋል። ወደ ትግበራ ሲገባ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በልማት ዕቅድ እና በማስፈጸሚያ ፕሮጄክቶች እየፈቱ መሄድን ይጠይቃል ብለዋል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን ነባራዊ ሁኔታዎችን እየተረዱ፣ ከችግሮች እየተነሱ መፍትሔ መስጠት ይገባል ነው ያሉት። የከተማ እና የገጠር ትስስርን በአግባቡ መከታተል እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። መንግሥት ለግብርናው ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል። ግብርና የመንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚታይበት መኾኑንም ተናግረዋል። የግብርናውን ምርት እና ምርታማነት የሚያሻሽሉ የግብዓት አቅርቦት በተደራጀ መንገድ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የግብርናው ባለቤት የኾነውን የግብርና መዋቅሩን እና አርሶ አደሮችን ስለ ፖሊሲው ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየረጅም ጊዜ የኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ!
Next articleየአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን 33ኛ ዙር የአድማ መከላከል ሠልጣኞችን እያስመረቀ ነው።