“ግብርናውን በአግባቡ ከተጠቀምነው ከእኛ አልፎ ሌሎችም የሚተርፍ አቅም አለ” መለስ መኮንን (ዶ.ር)

29

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቂያ መድረክ በባሕር ዳር ተካሂዷል። የግብርና ሚኒስትር ድኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) ፖሊሲው ሲዘጋጅ ያገባኛል የሚሉ አካላት ሁሉ እንዲሳተፉበት መደረጉንም ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የምርምር ተቋማት እና ሌሎች አካላት እንደተሳተፉበትም ተናግረዋል።

ፖሊሲው ወደ ታች የሚወርድበት የማስፈጸሚያ ስልት እንዳለውም ተናግረዋል። በርካታ ጉዳዮችን የያዘ እና የማስፈጸሚያ ስልቶችንም በተገቢው መንገድ የሚያመላክት ነው ብለዋል። የቀደመው ፖሊሲ ብዙ ምዕራፎችን ያስጓዘ፣ ብዙ ውጤቶችን ያስገኘ ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታው አሁን ላይ ፖሊሲ ለማሻሻል እንዲቻል ወረት እና ስንቅ የኾነው የቀደመው ፖሊሲ መኾኑን ገልጸዋል።

መካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች ለማካተት እና አዳዲስ ሃሳቦችን ለማመንጨት ዕድል እንደሰጠም አንስተዋል። ፖሊሲዎች እና የሕግ ማዕቀፎች በራሳቸው ግብ አይደሉም ያሉት ሚኒስትር ድኤታው ዋናው ግብ ፖሊሲውን ይዞ ተግባራዊ ማድረግ ነው ብለዋል። ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የመሪዎችን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅም አመላክተዋል።

ከሌሎች የልማት ፖሊሲዎች ጋር ተዛማጅነት ያለው መኾኑንም ገልጸዋል። ከተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። የተቋማት ቅንጅት ላይ ያለውን ክፍተት ሊፈታ የሚችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያን በግብርናው ዘርፍ በአፍሪካ መሪ የሚያደርግ እንደኾነም ተናግረዋል። የግብርናውን ምጣኔ ሃብት በተገቢው መንገድ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል። “ግብርናውን በአግባቡ ከተጠቀምነው ከእኛ አልፎ ሌሎችም የሚተርፍ አቅም አለ” ነው ያሉት።

አማራጮችን በመጠቀም ስለፖሊሲው እስከታች ድረስ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ባለሙያዎችን የማሰልጠን እና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። የአማራ ክልል በግብርናው እንደ ሀገር ካለው አስተዋጽኦ አንጻር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባልም ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ፖሊሲው የግብርናውን ዕድገት ወደፊት የሚስብ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleየረጅም ጊዜ የኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ!