“ፖሊሲው የግብርናውን ዕድገት ወደፊት የሚስብ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

30

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቂያ መድረክ በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ፖሊሲው ግብርናውን እንዴት ነው መለወጥ የሚችለው የሚለውን መልስ የሰጠ ነው ብለዋል። የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

ግብርናው የምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት እና መውጫ መንገድ ነው ያሉት ኀላፊው ወደ መዋቅራዊ ለውጥ ካልመጣን በስተቀር የሚፈለገው ዕድገት አይገኝም ነው ያሉት። ግብርናውን ማዘመን ኢንዱስትሪውንም ማዘመን እንደኾነ አንስተዋል። የግብርናውን ዕደገት ለማስቀጠል ፖሊሲውን በተገቢው መረዳት እና በአግባቡ መፈጸም እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

ከዚህ በፊት የነበረውን የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ምርትን እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በፍጥነት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ከድህነት መላቀቅ ላይ ማዕከል ያደረገ እንደነበር አስታውሰዋል። ብዙ ለውጦች እንደተመዘገቡበትም ገልጸዋል። አሁን ላይ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት መዋቅር ተቀይሯል፣ የሕዝቡ ፍላጎት እና ከግብርና የሚጠበቀው ተግባር እየሰፋ መጥቷል ያሉት ኀላፊው ይሄን የሚመጥን ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈልጓል ነው ያሉት።

ከአሁን በፊት የነበረው ፖሊሲ ለእንስሳት እርባታ ብዙ ትኩረት የሰጠ እንዳልነበር አንስተዋል። አዲሱ ፖሊሲ ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የተስማሙ እና የሚመጣጠኑ የልማት እሳቤዎችን ይዟል ነው ያሉት። አርብቶ አደሮችን፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃን እንዲኹም የእንስሳት እርባታን ትኩረት የሰጠ መኾኑንም ግልጸዋል።

“ፖሊሲው የግብርናውን ዕድገት ወደፊት የሚስብ ነው” ያሉት ኀላፊው አሁን ዓለም ከደረሰበት የምርት እና ምርታማነት ደረጃ እንድንደርስ የሚያደርግ ነው ብለዋል። በሚቀጥሉት ዓመታት የዓለምን የምርታማነት አማካይ ግብ ማሳካት የሚቻልበት ዕድል መኖሩንም ገልጸዋል። ፖሊሲው ክፍተቶችን የሚሞላ እና አዳዲስ ሀሳቦችን የጨመረ መኾኑን ነው የተናገሩት። ከቀደመው ፖሊሲ መቀጠል የሚገባቸው ሀሳቦች መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።

54 በመቶ የሚኾነውን የአማራ ክልል ምጣኔ ሀብት የሚሸፍነው ግብርናው ነው ያሉት ኀላፊው ያለውን አስተዋጽኦ ታሳቢ ያደረገ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ፖሊሲው ሕዝብን ከድህነት የሚያወጣ በመኾኑ የበርካታ አጋር አካላትን ድጋፍ እና ርብርብ ይጠይቃልም ብለዋል።

ፖሊሲውን በተመለከተ ቀጣይነት ያለው ውይይት እንደሚደረግበትም ገልጸዋል። ፖሊሲው ሲዘጋጅ በርካታ አጋር አካላትን ያሳተፈ፣ የምርምር ተቋማትን ግብዓት የወሰደ መኾኑን ተናግረዋል። ፖሊሲው ችግሮችን የለየ፣ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ሀሳቦችን የጨመረ በመኾኑ ጠንካራ እና ዘመኑን የዋጀ እንደኾነም አስረድተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቋሚ ቅጥር ማስታወቂያ!
Next article“ግብርናውን በአግባቡ ከተጠቀምነው ከእኛ አልፎ ሌሎችም የሚተርፍ አቅም አለ” መለስ መኮንን (ዶ.ር)