
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቂያ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) እና ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ዘመኑን የዋጀ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ማዘጋጀት ለዘርፉ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል። እንደ አዲስ የተዋወቀው የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከሌሎች ፖሊሲዎች ጋር የተሳሰረ መኾን እንደሚገባው ተናግረዋል። ግብርናውን ማዘመን፣ የከተማውን ማኅበረሰብ ታሳቢ ያደረገ እና ፍለጎቱ ጋር የሚጣጣም መኾን አለበት ነው ያሉት። እየሰፋ ያለውን ከተሜነት እና የከተማ ግብርናን ታሳቢ ያደረገ መኾን ይጠበቅበታልም ብለዋል።
የግብርናው ዘርፍ ትልቁ ማነቆ የመሬት አጠቃቀም ችግር ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ፖሊሲው የመሬት አጠቃቀምን በሚገባ መቃኘት አለበት ነው ያሉት። ለደን ልማት ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባውም ገልጸዋል። ፖሊሲው ለግብርና ምርምር ትኩረት መስጠት መቻል እንዳለበትም አንስተዋል። ወቅቱን የሚመጥን እና የነገን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ እንደሚያስፈልም ገልጸዋል።
የእንስሳት ሀብት ልማትን እና ተጠቃሚነትን በፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ማካተት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት። የፖሊሲ አተገባበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባም አመላክተዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት የተቀየሩ የፖሊሲ ማዕቀፎች ተተግብረው የኅብረተሰቡን ሕይዎት እየለወጡ ነው ብለዋል። በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያሳረፉ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እየተደረገ ያለውን ሽግግር ታሳቢ ያደረገ ሃሳብ እና ተግባር እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። ፖሊሲው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እየተደረገ ያለውን ሽግግር በጥንቃቄ ማየት አለበት ነው ያሉት። የገጠር እና የከተማ ትስስሩ በልዩ ትኩረት መታየት እንደሚገባውም አመላክተዋል። የከተማ እና የገጠር ትስስርን ፖሊሲው በግልጽ ማስቀመጥ አለበት ነው ያሉት።
ታዛማጅ ፖሊሲዎችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አመላክተዋል። ከተዛማጅ ፖሊሲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በግልጽ ማስቀመጥ እንዳለበትም አንስተዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩቱ ሥራ አሥፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ.ር) ሀገር አቀፍ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲው ከአሥራ ሁለት ተቋማት ጋር የተሳሰረ ተግባር እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ተቋማቱ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ በተገቢው መንገድ እንዲፈጸም አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ነው ያሉት። የከተማ እና የገጠር ትስስርም በፖሊሲው ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል። ገጠር እና ከተማ ተሳስረው አብረው የሚያድጉበትን አቅጣጫ ያመላክታል ብለዋል። አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እንዲያምርቱ፣ ግብዓት በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ ምርት እና ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ከአሁን ቀደም አርሶ አደሮች ተደራጅተው ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲያቀርቡ ይደረጋል፣ ኢንዱስትሪዎች ከፈለጉ ይገዛሉ፣ ካልፈለጉ ይተዋሉ፣ በዚህ መካከል አርሶ አደሮች ተጎጂዎች ነበሩ፣ አሁን ግን ይሄን አሠራር ያስተካክላል ነው ያሉት። አርሶ አደሮች እና ኢንዱስትሪዎች በሕግ ማዕቀፍ ተሳስረው ተጠቃሚ እንዲኾኑ ይደረጋል ብለዋል።
በፖሊሰው ለከተማ ግብርና ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል። የከተማ ግብርና ፍላጎት ከፍ እያለ እንደሚሄድም ተናግረዋል። የተቀናጀ አቅም መጠቀም እና ውጤት ማምጣት የሚያስችል መኾኑንም ገልጸዋል። የግሉን ዘርፍ፣ ማኅበረሰቡን እና መንግሥትን የሚያቀናጅ እና ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አንስተዋል።
የአፈር ጤንነትን የመጠበቅ ሥራም በፖሊሲው ትኩረት ተደርጎበታል ነው ያሉት። የግብርና ምርምርን እንደሚያሳደግም አንስተዋል። ለመስኖ ልማትም ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል። ፖሊሰውን በአግባቡ መፈጸም እና ማስፈጸም እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
