በአማራ ክልል ከ3 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮችን የግብርና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

28

ደብረ ብርሃን፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፑላ ኢትዮጵያ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ በግብርና መድኅን ላይ እየሠራ ይገኛል።

የፑላ ኢትዮጵያ የፊልድ ኦፕሬሽን ማናጀር ሮቤል አውጋቸው ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት የግብርና መድኅን ለአርሶ አደሮች አስተማማኝ ዋስትና ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል በስድስት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 122 ሺህ አርሶ አደሮች በሙከራ ደረጃ መተግበር የጀመረው የግብርና መድኀን አሁን ላይ ከ500 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ማቀፍ ስለመቻሉ አቶ ሮቤል ገልጸዋል።

በቀጣይ ይሄን ቁጥር ወደ 3 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ከ120 በላይ በሚኾኑ ወረዳዎች የግብርና መድኅንን ለማስጀመር እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከ3 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮችን የግብርና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራም ይገኛል።

ይሄንኑ ተግባር የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እንደ ሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ የግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች አርሶ አደሮች በዝናብ እጦት፣ በጎርፍ እና በተባይ ምክንያት በተደጋጋሚ ለኪሳራ ሲዳረጉ ይስተዋላል ብለዋል።

ከዚህ ዓይነቱ በእንስሳታቸው እና በምርታቸው ላይ ሊደርስ ከሚችል ኪሳራ ራሳቸውን ለመጠበቅ በአነስተኛ ወጭ የግብርና መድኅን ተጠቃሚ መኾን ያለው ጠቀሜታ ጉልህ ነው ብለዋል።

የግብርና መድኅን አርሶ አደሮች በተፈጥሯዊ ምክንያት በንብረታቸው ላይ እና በማሳቸው ላይ አደጋ ሊደርስባቸው ቢችል የካሳ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያስችል ዋስትና ስለመኾኑም ነው የተብራራው።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ከሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎች እና ከከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የግብርና መሪዎች እና ባለሙያዎች ተሳታፊ ኾነዋል::

ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ከእንግዲህ ዝናብ አይመታኝም”
Next articleዘመኑን የዋጀ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ማዘጋጀት ለዘርፉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።