”ከእንግዲህ ዝናብ አይመታኝም”

70

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለአረጋውያን እና ለሕጻናት የሠራቸውን ሥራዎች አስመርቋል። ቀኑን አስመልክቶም የፓናል ውይይት አድርጓል።

ኮሚሽኑ ያሠራውን የአንዲት አቅመ ደካማ ቤትን መኖሪያ ቤትን አስረክቧል። ቤቱ የተሠራላቸው እማሆይ ባንችአምላክ እጅጉ በባሕር ዳር ከተማ ሽምብጥ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በቦታው ለበርካታ ዓመታት ቢኖሩበትም አቅም የሌላቸው በመኾናቸው በፍሳሽ እና በጎርፍ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

አኹን ላይ ቤት ስለተሠራላቸው ”እንደ ሰው ኾኛለሁ፤ ከእንግዲህ ዝናብ አይመታኝም፤ አመሠግናለሁ” ብለዋል። የእማሆይ ባንችአምላክ ጎረቤት አቶ ሥራው ይኹን እማሆይ ረዳት የሌላቸው መኾናቸውን ጠቅሰው የሳጠራ ቤታቸውን በአዲስ ቤት የተካላቸውን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን አመሥግነዋል። ሌሎች ተቋማትም ተመሳሳይ ሥራ ቢሠሩ መልካም ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንችአምላክ ገብረማርያም ተቋማቸው የፕሮጀክት ገንዘብ ባይኖረውም ሰው ተኮር በኾኑ የልማት ሥራዎች ላይም መሳተፍ እንዳለበት ተወስኖ መሠራቱን ነው የገለጹት። የተቋሙ መሪዎች ቡድንም ኾነ ሁሉም ሠራተኞች ችግረኞችን ለመርዳት ላደረጉት ቀና ትብብርም አመሥግነዋል።

ቤት የተሠራላቸው አቅመ ደካማ እናት የአዕምሮ ሕመምተኛ እና ተፈናቃይ ልጆች ያሏቸው በችግር ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ብለዋል። ለአንድም ሰው ቢኾን ችግር ፈቺ ሥራ በመሥራታችን ደስተኛ ነኝ ነው ያሉት ኮሚሽነር ባንችአምላክ። ሌሎች ተቋማትም ችግረኛ ወገኖችን መርዳት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በግቢው የሕጻናት ማዋያ አሠርቶ ለሥራ ዝግጁ አድርጓል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአድማ መከላከል እና የመደበኛ ፖሊስ ምልምል ሰልጣኞች ከክልሉ አልፎ የሀገርን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ መኾናቸውን አቶ ደሳለኝ ጣሰው ተናገሩ።
Next articleበአማራ ክልል ከ3 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮችን የግብርና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው።