
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በብር ሸለቆ መሠረታዊ የውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተገኝተው የአድማ መከላከል እና የመደበኛ ፖሊስ ምልምል ሠልጣኞችን አበረታትተዋል።
የክልልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ እና የሕዝብ እና የመንግሥትን ፍላጎት አስመልክተው ለሠልጣኞች ማብራሪያም ሰጥተዋል። የሥልጠናውን ዓላማ፣ አስፈላጊነት እና ግቦች በተመለከተም ለሠልጣኞች ግልጽ አድርገዋል። ሥልጠናው በዋናነት ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ወታደራዊ ሥነ ምግባር የተላበሰ፣ በሥነ ልቦናው ያደገ እና በራስ አቅም የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ የሚችሉ ሠልጣኞችን ማፍራት እንደኾነም ነው አቶ ደሳለኝ የገለጹት።
ሠልጣኞች የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ ሕዝቡን ከገባበት ፈተና ለማላቀቅ እና ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር በማድረግ ረገድ ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ሠልጣኞቹ ከክልል አልፎ የሀገርን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ቁመና እና ዝግጁነት ላይ መኾናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል አቶ ደሳለኝ።
ከመደበኛ ሥልጠናቸው ባለፈ የስብዕና እና የአመለካከት ሥልጠናም ስለመሰጠቱ ነው የተናገሩት። ሠልጣኞቹ በጥሩ ቁመና፣ ቁርጠኝነት እና የሥነ ልቦና ዝግጁነት ላይ መኾናቸውንም አቶ ደሳለኝ ጣሰው አረጋግጠዋል። ሠልጣኞቹ በአመለካከት፣ በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የታገዘ ሥልጠና መውሰዳቸውን አሠልጣኞቹ ተናግረዋል።
በቀጣይ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት በመወጣት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
