“ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ግብርናውን በአዲስ መልክ ቃኝቶ ማሥተዳደር ያስፈልጋል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

33

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቂያ መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ድኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አዲስ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ስናስተዋወቅ ኢትዮጵያ እስካሁን የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ አልነበራትም ማለት አይደለም ብለዋል። አዲሱ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። ግብርና ካለበት ተልዕኮ አኳያ ተጨማሪ ሥራዎች እንዲሠራ ታስቦ የተዘጋጀ ፖሊሲ ነው ብለዋል።

እንደ አዲስ የሚተዋወቀው የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ፋይዳው ትልቅ መኾኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥር እየጨመረ ነው፣ ዕድገቱም ፈጣን ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የሀገሪቱን ሕዝብ ዕድገት ሊመጥን የሚችል ግብርና ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ምርት እና ምርታማነት ከሕዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር የተመጣጠነ መኾን ይገባዋል ብለዋል። የሕዝቡ አኗኗር እና አመጋገብም እየተቀየረ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ግብርናው ማምረት ብቻ ሳይኾን የአመጋገብ ባሕሪውን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫ መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ፖሊሲው እንዲሻሻል ካደረጉ ምክንያቶች አንደኛው መኾኑንም አንስተዋል። ለኢንዱስትሪው በቂ ግብዓት ለማቅረብም ለግብርናው ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት። “በቂ የኾነ የኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቀረብ እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ግብርናውን በአዲስ መልክ ቃኝቶ ማሥተዳደር ያስፈልጋል” ብለዋል።

በቀደመው ፖሊሲ የተረሱ እና ያልተካተቱ ሚናዎችን እንደሚጨምርም አንስተዋል። ግብርናችን በአነስተኛ አርሶ አደሮች ብቻ ተመርቶ ዕድገቱ ሊረጋገጥ አይችልም፣ ግብርናውን በተለመደው ማረሻ እና ሞፈር ብቻ ተጠቅመን ማሳደግ አንችልም ነው ያሉት። እስካዛሬ የተረሱትን የግሉ ዘርፍ ሚና ማጠናከር እንደሚጠበቅም አንስተዋል። ግብርናውን በአዲስ መልክ መምራት ካልተቻለ የግብርናውን ዕድገት ማስቀጠል እንደማይቻልም አንስተዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት የፖሊሲውን አቅጣጫዎች ተከትሎ እንደሚተገብርም ገልጸዋል። የአማራ ክልል በግብርናው ዘርፍ ግንባር ቀደም መኾኑንም አንስተዋል። የክልሉን ግንባር ቀደም ሚና ለማስቀጠል እና የኢንዱስትሪ ግብዓትን ለማሟላት ርብርብ እናደርጋለን ብለዋል። የአማራ ክልል ኢኮኖሚ በብዛት የሚሸፈነው በግብርናው መኾኑንም ተናግረዋል። ግብርናው ለክልሉ ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ ታሳቢ በማድረግ የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደጀን ወረዳ ለመኸር ምርት ከ77 ሺህ በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት እየሠራ ነው።
Next articleየአድማ መከላከል እና የመደበኛ ፖሊስ ምልምል ሰልጣኞች ከክልሉ አልፎ የሀገርን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ መኾናቸውን አቶ ደሳለኝ ጣሰው ተናገሩ።