ደጀን ወረዳ ለመኸር ምርት ከ77 ሺህ በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት እየሠራ ነው።

25

ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለ2017/18 የመኸር ምርት ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን አቅዶ እየሠራ መኾኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የደጀን ወረዳ የጤፍ ሰብል በብዛት ከሚመረትባቸው የምሥራቅ ጎጃም ዞን አካባቢዎች ተጠቃሽ ነው። ለ2017/18 የመኸር ሰብል ዝግጅት የምርጥ ዘር አቅርቦት እና የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት እየተከናወነ ሲኾን በሰባት ማኅበራት የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ተካሂዷል ያሉት የደጀን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስለሺ በልሁ ናቸው።

ለአርሶ አደሮች በቂ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት እየተሠራ መኾኑን የጠቀሱት ኀላፊው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ተሰራጭቷል ብለዋል። የግብዓት አቅርቦቱ በባለሙያ ታግዞ በተጠና እና የአርሶ አደሮችን ፍላጎት ባማከለ መንገድ በፍትሐዊነት እየተሠራጨ ስለመኾኑ አቶ ስለሺ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች የቀረበላቸውን ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም ለምርት እና ምርታማነት መጨመር በትጋት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። የደጀን ወረዳ አርሶ አደሮችም የእርሻ ዝግጅት ላይ መኾናቸውን ጠቅሰው የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እና የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዳለ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ያጋጥማቸው የነበረ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በዚህ ዓመት ሥጋት እንዳይኾንባቸው ስርጭቱ በዚሁ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሀገር አቀፍ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቂያ መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።
Next article“ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ግብርናውን በአዲስ መልክ ቃኝቶ ማሥተዳደር ያስፈልጋል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)