
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
ባለፉት ስምንት ወራት ከ18 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተመላክቷል። የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው ውስጥ የ”አሚናት፣ ሶፊያ እና ጓደኞቻቸው ልብስ ስፌት” ማኅበር አባላት ተጠቃሽ ናቸው።
የማኅበሩ ሰብሳቢ አሚናት ተፈራ ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሰባት ኾነው በማኅበር በመደራጀት በልብስ ስፌት ሥራ መሠማራታቸውን ገልጸዋል። ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የልብስ ማሽኞች፣ መሥሪያ ቦታ እና የመንቀሳቀሻ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
አሁን ላይ የሴቶች እና የወንዶችን አልባሳት በመሥራት ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ሥራውን በጀመሩበት ወቅት የገበያ ችግር ቢያጋጥማቸውም አሁን ላይ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። አልባሳትን በብዛት ለማስረከብም እየሠሩ መኾኑን ነግረውናል። በቀጣይ ሥራውን ለማስፉትም አቅደዋል።
በማኅበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በመስሪያ ቦታ እና በገንዘብ ችግር በፈለጉት መጠን እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸው መቆየቱን ነው የገለጹት።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ አብዱልሀሚድ ይመር በከተማ አሥተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት ለ28 ሺህ 228 ዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት ለ18 ሺህ 321 ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 8 ሺህ 971 የሚኾኑት በሀገር ውስጥ በቋሚነት ወደ ሥራ የገቡ ናቸው ነው ያሉት።
በአገልግሎት ዘርፍ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። የኢንዱስትሪ እና የግብርና ዘርፎች እና የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ሌሎች ዘርፎች ናቸው። 28 ሚሊዮን ብር መደበኛ በጀት እና 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ደግሞ የተዘዋዋሪ ብድር መሠራጨቱን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የተሠራጨ ብድር የአመላለስ ችግር በመኖሩ በአዲስ ሥራ እድል ለተፈጠረላቸው ዜጎች ለማሰራጨት እንደችግር አንስተዋል። ከዚህ በፊት ተላልፈው የነበሩ እና ውላቸውን ያጠናቀቁ መሥሪያ ቦታዎችን ለአዳዲስ ሥራ ፈላጊዎች የማስተላለፍ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
